19/06/2023
+ መልአኩ ነው +
ሰዓቱ ሌሊት ነው ፤ እንደ አጋጣሚ ሆኖ በዚያ ሌሊት መላው የቤተሰባችን አባል አምሽቶ እየተጫወተ ነው፡፡ ከዚህ የቤተሰብ ስብስብ መካከል ሳይገኝ የቀረው አንድ በወኅኒ ቤት የታሰረ ወንድማችን ብቻ ነበር፡፡ ድንገት ግን የጊቢው በር በተደጋጋሚ ተንኳኳና ሁላችንም ጨዋታችንን አቋረጥን፡፡ በሌሊት የሚያንኳኳው ማን ነው ?
ሠራተኛችን ሮጣ ሔደች:: ወዲያው ግን በሩን ሳትከፍተው ተመልሳ እየሮጠች መጣች፡፡ በደስታ ሰክራ ‹‹የታሰረው ልጃችን በር ላይ ቆሟል!›› ብላ ተናገረች፡፡ "በድምፁ አወቅኩት!› እያለች ዘለለች፡፡ ከሁኔታዋ የተነሣ ‹አብደሻል እንዴ!?› አላት ቤተሰቡ ሁሉ፡፡
እስዋ ግን በእርግጠኝነት ተናገረች! በቀን የታሰረው ልጅ በሌሊት ተፈቶ መምጣቱ ፈጽሞ ሊታመንን የማይችል ነገር ነው፡፡ ቤተሰቡ ሁሉ የታሰረው ልጅ መጣ ብሎ አላመነም፡፡ ባይሆን የመንግሥት ወታደሮች የቀረነውን ሊወስዱን ይሆን? ማን ሊሆን ይችላል? ብሎ ተብሰለሰለ:: በመጨረሻም የሁሉም ግምት አንድ ነገር ላይ አረፈ:: ሁሉም ሰው በአንድ ድምፅ አንድ ቃል ተናገረ "መልአኩ ነው!"
መልአኩ የሰው ስም አይደለም:: ቤተሰቡ የተስማማው "ደጅ የቆመው የታሰረው ልጃችን ሳይሆን እሱን ለመጠበቅ ከእግዚአብሔር የተሠጠው ጠባቂ መልአኩ ይሆናል›› ብሎ ነበር፡፡ የበሩ መንኳኳት አሁንም ስላልቆመ ቤተሰቡ ግር ብሎ ወጣና ተቻኩሎ በሩን ከፈተ፡፡ በደጅ የቆመው ግን እንደተባለው የታሰረው ልጅ ራሱ ነበር፡፡ ሁሉም ተደሰተ!!!
ይህ ገጠመኝ በአሁን ዘመን የተፈጸመ ነው ብዬ ብናገር ማን ያምነኛል? እውነት በሌሊት የቤታችን በር ሲንኳኳ መልአክ ነው ብለን እንገምታለን? ይህ ቤተሰብ ምን ዓይነት ቤተሰብ ነው?
በብዙዎቻችን አእምሮ ውስጥ መጀመሪያ የሚመጣው ጥርጣሬ ‹ሌባ ሊገባ ይሆን?› የሚል ስለሚሆን ዱላ ፍለጋ እናማትራለን፡፡ ወይ ደግሞ ሌሊቱ ወደ መንጋቱ እየተቃረበ ከሆነ ‹‹የምን መርዶ ሊያረዱኝ ይሆን? የቱ ዘመዴ ሞቶ ይሆን?› የሚል ጭንቀት ይፈጠራል፡፡
‹የሚያንኳኳው የእግዚአብሔርመልአክ ይሆናል› ብሎ የሚጠረጥር ሰው ግን በዚህ ዘመን ለማግኘት ያስቸግራል፡፡ እንዲህ ብሎ ግምቱን የሚናገር ሰው ከቤተሰባችንመካከል ቢገኝ እንኳን እንደ ዕብድ ልንቆጥረው እንችላለን፡፡ ታዲያ ይህን ገጠመኝ ከየት አመጣኸው ትሉኝ ከሆነ መልሱ ከመጽሐፍ ቅዱስ የሚል ነው፡፡
በሐዋርያት ዘመን ሔሮድስ የተባለው ንጉሥ ሐዋርያው ቅዱስ ጴጥሮስን ወኅኒ ቤት ውስጥ ወርውሮት ነበር፡፡ የቀሩት ደቀመዛሙርትና ክርስቲያኖች በዚያ ሰሞን ሲጸልዩ ከርመዋል፡፡ በአንድ ሌሊት በማርቆስ እናት ቤት ውስጥ ተሰብስበው አምሽተው ነበር፡፡ ድንገት የቤቱ በር ሲንኳኳ ሮዴ የምትባል የቤት ሠራተኛ ደጁን ልትከፍት ወጣች፡፡ ማነው ብላ ስትሰማ የቆመው እስረኛው ቅዱስ ጴጥሮስ መሆኑን በድምፁ አወቀች፡፡ ደስታ ግራ ሲያጋባት በሩን መክፈትን ረስታ ወደ ውስጥ ሮጠችና ጴጥሮስ መምጣቱን ተናገረች፡፡ እነርሱ ግን አላመኑአትም፡፡ ጤንነቷን ተጠራጥረው ‹አብደሻል› አሏት፡፡ እርግጠኛ ሆና ተናገረች፡፡ እነርሱ ግን መልሰው ‹‹የቆመው ጴጥሮስ ሳይሆን መልአኩ ነው፡፡›› አሉ፡፡ ይደንቃል የመጀመሪያዎቹ ክርስቲያኖች እንዲህ በር ሲንኳኳ ‹መልአክ ነው› ብለው የሚገምቱ መንፈሳዊያን ነበሩ፡፡ (ሐዋ. 12፡12-15)
ቅዱሳን መላእክት እኛ የሰው ልጆች ከመፈጠራችን ቀድመው የተፈጠሩ ታላቅ ወንድሞቻችን ናቸው፡፡ እንዲያውም ምድርና የሰው ልጅ ሲፈጠር ደስ እያላቸው ‹‹እልል›› ይሉ ነበር፡፡ (ኢዮ. 38፡6) ቅዱሳን መላእክትን እግዚአብሔር ለእንዳንዳችን ጠባቂዎች አድርጎ ሠጥቶናል፡፡ ከክርስቶስ እግር ሥር ቁጭ ብለው የተማሩት ቅዱሳን ሐዋርያት ስለ መላእክት ጠባቂነት ጋር ይህን ያህል እምነት ከነበራቸው እኛም የመላእክቱን ጠባቂነት ማመን ለዚህ ዘመን ክርስቲያኖችም ምን ያህል ይገባን ይሆን? ቅዱሳን መላእክት በክርስትና ሕይወት ለሚኖርሰው ሁሉ የመላእክት ረዳትነት እጅግ አስፈላጊ ነው፡፡ ለሁሉ ብርታት የሆነው ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እንኳን በሥጋው ወራት በተያዘባት ምሽት ሲጸልይ ‹‹ከሰማይም መጥቶ የሚያበረታው መልአክ ታየው›› ተብሎ ተጽፏል፡፡ (ሉቃ. 22፡43) ይህም ቀርበው አገለገሉት‹ለከ ኃይል› እያሉ አመሰገኑት ማለት ሲሆን ለእኛም የመላእክት ርዳታ አያስፈልገኝም እንዳንል የሚያስተምረን ነው፡፡
ቅዱሳን መላእክት በምድር የሚሆነውን ያውቃሉ:: (2 ሳሙ 14:20) በበደላችን ስንጸጸት "ኃጢአትህ ተሠረየችልህ" ይላሉ (ኢሳ 6:7) በክፋታችን ጸንተን ከቀጠልን ደግሞ "ይቅር አይሉም" (ዘጸ 23:20)
ስለእኛ በእግዚአብሔር ፊት ቆመው "የማትምራቸው እስከ መቼ ነው?" ብለው ያማልዳሉ:: (ዘካ 1:12)
ባለንበት ዘመን በዓለም ሁሉ በበሽታ የሚሠቃየው ብዙ ነው:: በሕመም ለሚሠቃየው ሁሉ
"መልአክ ቢገኝለት እየራራለት [ለእግዚአብሔር] ፡— ቤዛ አግኝቻለሁና ወደ ጕድጓድ እንዳይወርድ አድነው፡ ቢለው፥ ሥጋው እንደ ሕፃን ሥጋ ይለመልማል፤ ወደ ጕብዝናውም ዘመን ይመለሳል" ኢዮ 33:23-25
ዲያቆን ሄኖክ ኃይሌ
ሰኔ ሚካኤል - 2007 ዓ ም የተጻፈ