23/07/2022
Bless and happy birthday father!!!
ግርማ አላቸው፡፡ ባለ ግርማ ስራ ሰርተዋል፡፡ መልካም ቱሩፋታቸውን ያገኘነው በመወለዳቸው ነው፡፡ ጃ እንኳን ተወለዱ፡፡
***
(ሄኖክ ስዩም ~ድሬ ቲዩብ)
ዛሬ የአፍሪካ አባት ልደት ነው፡፡ ግርማዊነታቸው ስማቸው ገናና ክብራቸው የናኘ ታላቅ ንጉሥ ናቸው፡፡ በልደታቸው ቀን ታላላቅ ሥራዎቻቸውን እናነሳለን፤ ዛሬም እሳቸው ያቆሙት ሆስፒታል የሀገሩ ትልቅ ነው፡፡ ዛሬም እሳቸው ያነጹት ቲያትር ቤት አንጋፋው ኾኖ በክብር ይኖራል፡፡
ግርማ አላቸው፡፡ ባለ ግርማ ስራ ሰርተዋል፡፡ መልካም ቱሩፋታቸውን ያገኘነው በመወለዳቸው ነው፡፡ ጃ እንኳን ተወለዱ፡፡
ለአዲስ አበባ ያኖሩት ማዘጋጃ እንኳን ለማነጽ ለማደስ አስደንግጧል፡፡ የመዲናይቱ ውብ ህንጻዎች የእሳቸው ዘመን አሻራዎች ናቸው፡፡ ሀገር የአፍሪካ ኩራት የሆነ አየር መንገድ እንዲኖራት መሰረት ጥለዋል፡፡
ንቁ ንጉሥ ናቸው፡፡ ባለ ቤተ መጻሕፍቱ፡፡ ወመዘክርን በዘመናቸው ተከሉ፤ ደግሞ ቤታቸውን ለትምህርት ቤት ሰጡ፡፡ ዛሬም በስማቸው የጀመሩት ዩኒቨርሲቲ የሀገሩ አውራ ነው፡፡ አውራው የአፍሪካ ንጉሥ፤ ኬኒያ ቢደርሱ ናይሮቢ በስማቸው በራፍ ፍጥነው የሚያልፉበት መንገድ የሚያወሳቸው፡፡
ኢትዮጵያ የአፍሪካን አብሮነት ስትወልድ አባት ነበሩ፤ ኢትዮጵያ ዓለም ጉባኤ ስትገባ እጇን ይዘው ወሰዷት፡፡ ኢትዮጵያ ለነጻነት ከጥቁር ሁሉ ጎን ስትቆም ጃ የአፍሪካ አባት እስኪባሉ አህጉር ተመካባቸው፡፡ ካረቢያን ድረስ የተቀደሰ ስም ያዙ፡፡
ታሪክ የመጨረሻው ሰለሞናዊ ንጉሥ ይላቸዋል፡፡ ዛሬ በስማቸው የሚምል ባይኖርም የሚማልበት አሻራ ትተው ያለፉ መሆናቸውን የሚክድ የለም፡፡ ወርቃማው ዘመን የሚባለውን ተክለውታል፡፡
ጨለማ የሚባሉ የታሪክ ምዕራፎችን ያስተናገደው የግዛት ዘመናቸው ባበሩት ብርሃን ተገፏል፡፡ በዘመናቸው ከተከሰተው ከባድ ድርቅ ይልቅ ዛሬ ድረስ መታየት የቻለው ሰፋፊ የእርሻ ልማት ስራቸው ነው፡፡
በውትድርና፣ በባህር ትራንስፖርት፣ በቴክኖሎጂ ብዙ ደክመዋል፡፡ የተጀመረ አስቀጥለው አዳዲሱን መሰረት ጥለው ዛሬ ላለችዋ ኢትዮጵያ አያሌ ቱሩፋት አኑረዋል፡፡ ለዚህም ነው ባይወለዱ ብዙ የሚቀርብን ነገር ነበር የምንለው፤ ብዙ፡፡
ራስ ተፈሪ፣ ንጉሥ ተፈሪ፣ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ፣ ንጉሠ ነገሥቱ በዛሬው ቀን በኤጀርሳ ጓሮ ተወለዱ፡፡
የታላቁ ጦረኛ የአድዋው ጀግና የራስ መኮንን ልጅ፤ የውቧ እቴጌ የመንን ባል፣ የሬጌው ሙዚቃ አዝማች ሽቅርቅሩ ንጉሥ፤
አበባ ጃንሆይ፤
የወንዶ ገነቱ ዋናተኛ፣ የመልካሳው ወንዝ አፍቃሪ፣ የቤዛዊቱ ኮረብታ ወዳጅ፣ የራስ ግንቡ ጥቁር እንግዳ፣ የኤረር ጎታው ኩሩ ሰው፣ የቁልቢው ተሳላሚ፣ የምስራቁ የታህሳስ ሰው፤ የአፍሪካ አንድነቱ ጌጥ፤ የማይጨው ጀግና ዘማች፤ የሊግ ኦፍ ኔሽኑ ተናጋሪ፣
ደግሞ ተፈጥሮ አፍቃሪው። የአዋሽ ፓርኩ ጎብኚ፣ የአጆራው ልበ ደንጋጭ፣ የጢስ አባዩ አስጎብኚ፣ የአክሱም ጽዮን ስዕለት አድራሽ፣ የሸከና ሁሴን ዘያሪ።
እሳቸው እንዲህ አሉ፤ አሁን የእኛ ታሪክ እዚህ ላይ ያበቃና የእናንተ ታሪክ ይጀምራል፡፡ ጀምረን ቀጥለናል፡፡ የማይረሱ ብዙ ቱሩፋቶችዎን አስበን ግን እንኳን ተወለዱ እንላለን፡፡
አባባ ጃንሆይ፤ እንኳን ተወለዱ፡፡