25/12/2024
በደቡብ ኢትዮጵያ ክልላዊ መንግስት በደቡብ ኦሞ ዞን በማሌ ወረዳ ከሚገኙ በርካታ ተፈጥሯዊ :ባህላዊና ታሪካዊ የቱሪዝም መስህቦች የተወሰንቱን በፅሁፍና በፎቶ እናስቃኛችሁ!
የማሌ ወረዳ በደቡብ ኦሞ ዞን ከሚገኙ ወረዳዎች አንዱ ሲሆን በሥሩ 21 ገጠር ቀበሌያትና 7 ታዳጊ ማዘጋጃ ከተማ ቀበሌያት በአጠቃላይ በ28 ቀበሌያት ይኖራሉ፡፡
በ1999 ዓ/ም በተደረገው አገር አቀፍ ሕዝብና ቤቶች ቆጠራ ውጤት መሠረት የብሔረሰቡ ሕዝብ ብዛት በ2016 ዓ.ም መጨረሻ ወንድ 69,529 ሴት 67,809 ድምር 137,338 እንደሆነ ይገመታል፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ የተለያዩ አካላት ለክትባት እና ለሌሎች አገልግሎት የተጠቀሙት መረጃ የሚያሳየው አጠቃላይ የህዝቡ ቁጥር 201,168 እንደሆነ ያረጋግጣሉ፡፡
የማሌ ወረዳ መልክአ ምድራዊ አቀማመጥ ከፊል ሜዳማ እና ተራራማ ሲሆን 80 በመቶ ቆላማ እና 20 በመቶ ወይና ደጋ የአየር ጸባይ እንዳለው የተለያዩ የመረጃ ምንጮች ያትታሉ፡፡
ወረዳው ባህላዊ፣ ታሪካዊና፣ ተፈጥሮኣዊ እንዲሁም ሃይማታዊና የመሳሰሉትን ጨምሮ የቱሪዝም ሀብቶች መገኛ ነው፡፡ በወረዳው ከሚገኙ የቱሪዝም መስህቦች ጥቂቶቹ፡-
ሀ) የወንዳቃሪ ጥብቅ ደን፡
በማሌ ወረዳ በባህል ደረጃ የሚጠበቁ ባህላዊና ታሪካዊ ደኖች የማይነኩ የእግዚአብሔር ጫካዎች ተብለው ከማንኛውም ንክኪ የተጠበቁ ብዙ ደኖች አሉ፡፡ ከባህላዊ ደንብ መሥሪያ ደኖች ዬቤሪ ደን፣ ዱኡፓ፣ ካርካሮ እና ሌሎችም ይገኙበታል፡፡
የወንዳቃሪ ጥብቅ ደን የወረዳው ማዕከል ከሆነችው ሌሞጌንቶ 17 ኪ.ሜ ላይ ቡይላንሣና ቲኪቦኮ በሚባሉ ቀበሌያት መሀል የሚገኝ የተፈጥሮ ጥብቅ ደን ነው፡፡
ለ) የቦሽኮሮ ደብረ ኢዮር ቅዱስ ሚካኤል ቤተ ክርስቲያን፡
የቦሽኮሮ ቅዱስ ሚካኤል ቤተ ክርስቲያን በቀደምት አባቶች በ1901 ዓ/ም የተመሰረተ ከመቶ ዓመት በላይ ዕድሜ ጠገብ ታሪካዊና ሃይማኖታዊ መስህብ ነው፡፡
የቤተ ክርስቲያቱ ታሪክ አዋቂዎች ለማሌ ማህበረሰብ የመጀመሪያው የሃይማኖት ትምህርት የሰሙበት እንደሆነ ይናገራሉ፡፡
ሐ) ፃባላ (ፃዋላ) ፍልውሃ፡
ከወረዳው ማዕከል ሌሞ ጌንቶ 22 ኪ.ሜ ርቀት ላይ ባለች ቡይላንሳ ቀበሌ የሚገኝ የ 2 ሜትር ያህል ጥልቀት እና እና የ 1.5 ሜትር ያህል ስፋት ያለው የአካባቢው ነዋሪዎች ታጥበውበት ለመፈወሻነት የሚጠቀሙት ነው፡፡
የፍልውሃው አገልግሎት በአካባቢውና በዙሪያው የሚገኙ ግለሰቦች በተለያዩ በሽታዎች በተለይም በሰውነት ላይ የሚወጣ የቆዳ በሽታ፣ ዕጥ፣ የሰውነት እብጠት ያለባቸው እንደሚፈወሱበት ይናገራሉ፡፡
መ) ፃንዳራ ማራኪ የመሬት ገጽታ፡
ፃንዳራ በጌራጋዶ ቀበሌ የሚገኝ ማራኪ የመሬት ገጽታ ነው፡፡
ይህ የመሬት ገጽታ ማንኛውም ዓይነት የሰው ንክኪ እንዳልመሠረተው የሚናገሩት የአካባቢው ነዋሪዎች ስናውቀውና በታሪክ ስንሰማ እንደዚህ እንደሆነ እንጂ እንዴት እንደተፈጠረ አናውቅም በማለት ይናገራሉ፡፡
ሠ) ሶኦዞ ኮኖ ፏፏቴ፡
ከከፍታ ተወርውሮ ሲወርድ ጥስና ቀስተ ደመና የሚሰራ በዒርቦ ቀበሌ የሚገኝ ትልቅ ፏፏቴ፡፡
በማሌኛ ቋንቋ “ሶኦዞ” ማለት የፏፏቴው መገኛ የአካባቢው ስም ሲሆን “ኮኖ” ማለት ደግሞ ጎተራ ማለት ነው፡፡ የስያሜው አሰጣጥ ምንነቱን የአካባቢው ነዋሪዎች የፏፏቴው አወራረድ የጎተራ መልክ ካለው አለት መሀል አልፎ ሰለሆነ ያንን ተከትሎ የተሰጠ ስያሜ እንደሆነ ይናገራሉ፡፡
ረ) የመቃብር ላይ ትክል ድንጋዮች /Gravesotnes/:
ጋማጉፄ ትክል ድንጋይ በጎሎ ቀበሌ፣ ጋምቦ ትክል ድንጋይ በአዦ እና ሌሎችም ትክል ድንጋዮች ይገኛሉ፡፡
የፅሁፍና ፎቶ ምንጭ :የማሌ ወረዳ መንግሥት ኮሚኒኬሽን : ደ/ኦ/ዞ/ባ/ቱ/መምሪያ - ከፎቶ ማህደር