17/04/2024
የሚዛን አማን ከተማ አስተዳደር ማዘጋጃቤታዊ አገልግሎት ማዘመኛ ዲጂታላይዝ ሶፍትውየር ሲስተም ማስጀመሪያ መርሃግብር ተካሄደ።
ሚዛን አማን ሚያዚያ 9/2016 ዓ/ም የሚዛን አማን ከተማ አስተዳደር ማዘጋጃቤታዊ አገልግሎት ማዘመኛ ዲጂታላይዝ ሶፍትዌር ሲስተም ማስጀመሪያ መርሃግብር ተካሄደ።
ማዘጋጃ ቤቱ በ2015 ዓ/ም ከመሃመድ አሚን አባቡና ጓደኞቹ የሶፍትዌር ዲዛይንና ልማት ስራ ኢንተርፕራይዝ ጋር የመግባቢያ ስምምነት በመፈራረም የተቋሙን መረጃዎች ለማዘመን ወደ ሲስተም የማስገባት ስራዎች ሲሰሩ መቆየታቸው ተገልጿል።
በተቋሙ አገልግሎቱን ያስጀመሩት የደቡብ ምእራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልላዊ መንግስት ከተማልማትና ኮንስትራክሽን ቢሮ ሃላፊ ተወካይና የመሬት ልማት ማናጅመንት ዘርፍ ሃላፊ አቶ ጫናቸው ወንድሙ፣ የሚዛን አማን ከተማ ከንቲባ አቶ ግሩም ተማም፣ በከተማና መሰረተ ልማት ሚኒስቴር የከተማ አመራር አቅም ግንባታ ዴስክ ሃላፊ አቶ ተካ በቀለን ጨምሮ የክልሉ ከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ቢሮ የዘርፍ ሃላፊዎች፣ የማዘጋጃ ቤት ስራ አስኪያጆችና ከፍተኛ የመንግስት የስራ ሃላፊዎች ተገኝተዋል።
ፕሮግራሙን አስመልክቶ ገለጻ ያደረጉት የሚዛን አማን ከተማ ማዘጋጃ ቤት ስራ አስኪያጅ አቶ አሰፋ ቤሪ ተቋሙ ከወረቀት አሰራር በመውጣት የአገልግሎት አሰጣጥ ማዘመኛ ሶፍትዌር በመጠቀም ዘመናዊ አሰራር ለመከተል የቅድመ ዝግጅት ስራዎች ሲሰሩ መቆየታቸውን አብራርተዋል።
በዋና ማዘጋጃ ቤትና በቀበሌ ማዘጋጃ ቤቶች መረጃዎችን ወደ ሲስተም የማስገባት ስራዎች ሲሰሩ መቆየታቸውን የገለጹት ዋና ስራ አስኪያጁ በዚህም ከ20 ሺህ በላይ ህጋዊ ሰነድ ያላቸውን መረጃዎች ወደ ሲስተም በማስገባት በዛሬው እለት አገልግሎቱን ማስጀመር ተችሏል ብለዋል።
ሲስተሙ በማዘጋጃ ቤት ዘመናዊ አሰራር ለመዘርጋት የሚያስችል ከመሆኑም በላይ የፋይል መጥፋት፣ መበላሸትና የባለጉዳይ መጉላላትን ጨምሮ ብልሹ አሰራሮችን የሚያስቀር መሆኑ ተገልጿል።
የተቋሙ የአገልግሎት አሰጣጥ ስታንድራድ ምልከታ የተካሄደ ሲሆን ከመረጃ ክፍል ጀምሮ የቡድን መሪዎችና ስራ አስኪያጅ ድረስ የተሳሰረ ሲስተም መዘርጋቱ ተጠቁሟል።
ማዘጋጃ ቤቱ በተወሰኑ የስራ ክፍሎች ደንበኞችን ለማገልገል በሚያስችል መልኩ ለተመሳሳይ አገልግሎት የሚሰጡ ባለሙያዎች ተመሳሳይ አለባበስ እንዲከተሉ የጀመራጀው ስራዎች መኖራቸው ተጠቅሷል።