25/01/2020
ኢ/ር ታከለ ኡማ በመሃል አዲስ አበባ ጎተራ አከባቢ የሚገነባውን የአሚባራ መንደር ግንባታ በዛሬው ዕለት አስጀምረዋል፡፡
ይህ ዘመናዊ የመኖሪያ መንደር በአፋር ባለሃብቶችና በከተማ አስተዳደሩ በጋራ የሚገነባ ሲሆን የ35ሺ ካሬ ሜትር ነባር ይዞታቸው ላይ የከተማ አስተዳደሩ 15ሺ ካሬሜትር ይዞታ በመጨመር በድምሩ በ50 ሺ ካሬሜትር መሬት ላይ የሚገነባ ይሆናል፡፡
ዘመናዊ የመኖሪያ መንደሩ በውስጡ ከ450 በላይ የመኖሪያ አፓርትመንቶችን ጨምሮ የገበያ ማዕከላት፣ ሆቴል፣ ተመራጭ የመዝናኛና የንግድ ማዕከል ፣ ኣረንጓዴ ስፍራዎች እና የአፋር ባህል ማዕከልን ያካተተ ነው፡፡
ግንባታው በ11 ቢሊዮን ብር የሚከናወን ሲሆን ከ10 ሺ በላይ ለሚሆኑ የከተማችን ወጣቶች ቋሚና ጊዜያዊ የስራ ዕድል የሚፈጥር ይሆናል፡፡
ግንባታ በማስጀመሪያ መርሃ ግብሩ ላይ ንግግር ያደረጉት ኢ/ር ታከለ ኡማ በከተማዋ ውስጥ ያለውን የቤት ችግር ለመቅረፍ የከተማ አስተዳደሩ በቀጣይነትም ሌሎች ባለሃብቶችን በማስተባበር መሠል ፕሮጀክቶችን እንደሚጀምር ተናግረዋል፡፡
በአፋር ባለሃብቶች ለሚገነባው የአሚባራ ዘመናዊ የመኖሪያ መንደር የከተማ አስተዳደሩ አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግም ኢ/ር ታከለ ጨምረው ገልጸዋል፡፡
በግንባታ ማስጀመሪያ መርሃ ግብሩ ላይ ኢ/ር ታከለ ኡማን ጨምሮ ፣ የኢፌድሪ የኮንስትራክሽንና የከተማ ልማት ሚኒስቴር ኢ/ር አይሻ መሃመድ ፣ የአፋር ተወላጆችና ሌሎች የከተማዋ ነዋሪዎች ተሳታፊ ሆነዋል፡፡
በተባበሩት አረብ ኤሚሬቶችና በቻይና ኩባንያዎች
ከሚገነቡት ዘመናዊ የመኖሪያ መንደሮች በተጨማሪ ሌሎች 8 ዘመናዊ የመኖሪያ መንደሮች ግንባታ የሃገር ውስጥ ባለሃብቶችን በማሳተፍ በቅርቡ ወደ ስራ ለመግባት የከተማ አስተዳደሩ እየሰራ እንደሆነ ይታወቃል፡፡