10/08/2022
✅የቅዱስ ገላዉዲዎስ ቤተክርስቲያን :-
በጎንደር ክፍለሀገር ደብረታቦር አውራጃ በደራ ወረዳ በአስደናቂ ነገሮች የተሞላውን የቅዱስ ገላውዲዎስ ቤተክርስቲያን ታሪክ
የቅዱስ ገላውዲዎስ ቤተ-ክርስቲያን በገላውዲዎስ ቀበሌ አስተዳደር ስር የሚገኝ ሲሆን ቀበሌው ስሙን ያገኘው በዚሁ ቤተክርስቲያን ስም እንደሆነ ይነገራል ፡፡ የሰማእቱ ቅዱስ ገላውዲወስ ቤተ-ክርስቲያን በጎንደር ክፍለሀገር ደብረታቦር አውራጃ በደራ ወረዳ በገላውዴዎስ ቀበሌ ይገኛል፡፡ ይህ ቤተክርስቲያን ከአርብ ገበያ ከተማ ወደ እስቴ ሲጓዙ ከ10 ኪሎ ሜትር ጉዞ በኃላ ይገኛል ፡፡ 4 ማዕዘን ቅርፅ ያለውና 3 ጉልላት ያሉት የገላውዴዎስ ቤተክርስቲያን የተመሰረተው ከ1540-1559 እ.ኤ.አ በኢትዮጵያ በነገሱት በአፄ ገላውዴዎስ ዘመነ መንግስት ነው ፡፡ የስሙ አወጣጥ ከዚሁ ጋር ተያይዞ እንደሆነ ድርሳናትም ይናገራሉ ፡፡ የአፄ ልብነድንግል ልጅ የሆኑት ንጉስ ገላውዴዎስ የግራኝ አህመድ ግፍ ባንገፈገፋቸው ጊዜ ብዙ ሰራዊት ብዙ ግመሎችና የሰማዕቱ ገላውዴዎስን ታቦት ይዘው ዘመቱ፡፡ ወደ አሁኑ የገላውዴዎስ ቀበሌ ከአሁኑ የገላውዴዎስ ቤተክርስቲያን ከተመሰረተበት እረጅም ተራራ ላይ በደረሱ ጊዜ ግመሎቻቸው ደከሙባቸው የያዙትን ጦር ይዞ መቀጠል ተስኗቸው ለያዙት ታቦተ ብፅአት ገቡ (ስለት ተሳሉ) #“ግራኝን ድል ለማድረግ ብታበቃኝ ቤተክርስቲያንክን ከዚህ ቦታ ሰርቸ አስቀምጣለሁ” # የሚል ፡፡ የደከሙ ግመሎቻቸውንና ሰራዊታቸውን ይዘው ወደ ሰሜን ጎንደር አቀኑ ፡፡ በለስም ቀናቸውና በአሁኑ ሰዓት “ግራኝ በር” በተባለው ቦታ ላይ ሲደርሱ ግራኝ
አህመድን ድል አደረጉ፡፡ ቃላችውንም ሳያፈርሱ በቦታው የታቦተ ገላውዴዎስ ቤተክርስቲያን ተከሉት ፡፡ ብዙ ግመሎችና አገልጋዮችን የስጦታ እቃዎችንም
በዚያው አስቀምጠዋል ፡፡ በቦታው ረጅም ዘመን ያላቸው ታሪካዊ ቅርሶች፣ንዋየ ቅዱሳትና በተለያዩ ነገስታት የተበረከቱ ስጦታዎች ይገኛል ፡፡ ከነዚህም መካከል የአፄ ቴዎድሮስ ምንጣፍና መከዳ
(ትራስ) ፣ የአጼ ገላውዴዎስ ቀንደ መለከትና ሰናፊ (ፈረስ ላይ ሲቀመጡ የሚለብሱት) የግራኝ አህመድ ካባ ዋና ዋናዎቹ ናቸው ፡፡
ቤተክርስቲያኑን ልዩ የሚያደርጉት ሁኔታዎች፡-
*በሌሎች ቤተክርስቲያን የቀብር ስነ-ስርዓት የሚካሄደው ከታላላቅ ሰዎች ውጭ ከቤተክርስቲያኑ ቅጥር ግቢ ውጭ ነው በገላውዲዴዎስ ቤተክርስቲያን ግን ከዚህ ለየት ይላል ፡፡ ማንኛውም ሰው የሚቀበረው በቅጥሩ ውስጥ ነው እንዴት ይሉ ይሆናል ሴቶች በቤተክርስቲያን ስርዓት በስተደቡብ ወንዶች ደግሞ በስተሰሜን የቀብር ስርአት ይፈፅማል ፡፡ በሳጥን ወይም በግንብ (በኃውልት) መቅበር ግንአይፈቀድም ፡፡ ነገር ግን የቀብር ጥበት ብሎ ችግር በቤተክርስቲያኑ አይታሰብም። ለምን ቢሉ የአንድ ሰው እሬሳ ከተቀበረ ከወር በኃላ የት እንደሄደ አይታወቅም፡፡
*ሁለተኛው አስገራሚ ጉዳይ ደግሞ ቤተክርስቲያኑ ሲመሰረት አብራ የገባችና አሁን ድረስ በግቢው በር በቀኝ በኩል የምትገኝ ንብ ናት ፡፡ የሚያስገርመው እንደ ሐይማኖት አባቶች አባባል ይህን ያህል እድሜ ስትቆይ የማትራባ መሆኗ ነው ፡፡የምትሰጠውን ማር ለህሙማን ፈውስ ተብሎ ብዙዎቹ እንደሚጠቀሙበት ብዙ ነዋሪዎች ይናገራሉ ፡፡
የቅዱስ ገላውዲዎስክብረ-በአል ታህሳስ 11 በደማቅ ሁኔታ ይከበራል ፡፡