11/01/2023
ጎንደር የጥምቀትን በዓል ለማክበር አስፈላጊውን ዝግጅት አድርጋለች - አቶ ዘውዱ ማለደ የጎንደር ከተማ ከንቲባ
የጥበብና ኢትዮጵያዊነት መድመቂያ የሆነችው ጎንደር የጥምቀት በዓልን ለማክበር አስፈላጊውን ዝግጅት አድርጋለች ሲሉ የከተማዋ ከንቲባ ዘውዱ ማለደ አስታወቁ፡፡
አቶ ዘውዱ ጎንደር ከተማ የጥምቀት በዓልን ለማስተናገድ ያደረገችውን ዝግጅት አስመልክተው መግለጫ ሰጥተዋል፡፡፡
በመግለጫቸውም የባሕል፣ የጥበብና የኢትዮጵያዊነት መገለጫ የሆነችው ጎንደር ከሀገር ውስጥና ከተለያዩ የዓለማችን ክፍሎች እንግዶቿን ተቀብላ የጥምቀት በዓልን በደመቀ ሁኔታ ለማክበር መዘጋጀቷንም ጠቁመዋል፡፡
በከተማዋ ከጥር 6 ቀን 2015 ዓ.ም ጀምሮ “የባሕል ሣምንት” እንደሚከበር ነው ከንቲባው የተናገሩት፡፡
በዚህም መሠረት የአፄ ቴዎድሮስ የልደት በዓል፣ ሁሉንም የሚያሳትፍ ታላቅ ሩጫ፣ ምስጋናና እውቅና ፣ የታሪክና ወ መዘክር ቤተ ንባብ ግንባታ የመሰረት ድንጋይ ማስቀመጥ መርሐ ግብር ይከናወናል ብለዋል፡፡
በተጨማሪም የአዝማሪ ፌስቲቫል፣ የቁንጅና ውድድር፣ ኤግዚቢሽንና ባዛር፣ የፋሲለደስ ት/ቤት 80ኛ ዓመት በዓልና የገቢ ማሰባሰቢያ እንዲሁም የንጉሥ ዕራትና የፎቶ አውደ ርዕይ መርሐ-ግብሮች እንደሚካሄዱ ጠቁመዋል፡፡
የጥምቀት በዓል ሃይማኖታዊ ሥርዓት ደግሞ ከጥር 10 ጀምሮ እንደሚቀጥል ጠቁመው÷ በሁነቱም እንግዶችን የማስተናገድ ባሕልና ወግ ተጠናክሮ ይቀጥላል ነው ያሉት፡፡
እንደ መንገድ፣ ውሃና መብራትን የመሳሰሉ ልዩ ልዩ የመሰረተ ልማት አቅርቦቶችና አገልግሎቶች እየተሟሉ መሆናቸውንም አብራርተዋል፡፡
በበዓሉ ሰሞን ችግሮች እንዳይፈጠሩ ኅብረተሰቡ ከጸጥታ አካላት ጋር በመተባበር እንዲሰራም አሳስበዋል፡፡
በአገልግሎት ሰጪ ተቋማት በቂ ዝግጅት መደረጉንና የአልጋ እጥረት እንዳይከሰትም ተጨማሪ ዘመናዊ የእንግዶች ማረፊያ ድንኳኖች እየተዘጋጁ መሆናቸውን አስረድተዋል ሲል ፋና ዘግበዋል፡፡
•~•~•
"የጎሃ ቃልኪዳናችን የከፍታችን ልክ -ቃላችንን ፈፅመን ከፍታው ላይ እንገናኝ"