12/09/2013
የምሥራቅና ደቡብ አፍሪካ የንግድና ልማት ባንክ የሆነው ፒቲኤ ባንክ ለኢትዮጵያ አየር መንገድ ሠራተኞች መኖሪያ ቤቶችና ለሐበሻ ሲሚንቶ ፋብሪካ አክሲዮን ማኅበር ግንባታ የሚውል 100 ሚሊዮን ዶላር ብድር ፈቀደ፡፡
የኢትዮጵያ አየር መንገድ እየገነባው ላለው የሠራተኞች መኖሪያ ቤቶች የሚውል 40 ሚሊዮን ዶላር የተፈቀደለት ሲሆን፣ የብድሩ የመጀመሪያ ዙር 22 ሚሊዮን ዶላር ስምምነት ባለፈው ሰኞ በካፒታል ሆቴል ተፈርሟል፡፡ ስምምነቱን የፈረሙት የፒቲኤ ባንክ ፕሬዚዳንት ኢትዮጵያዊው አቶ አድማሱ ታደሰና የኢትዮጵያ አየር መንገድ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ተወልደ ገብረ ማርያም ናቸው፡፡ አየር መንገዱ ለድርጅቱ ሠራተኞች መኖሪያ የሚሆኑ 1,192 ቤቶችን በቦሌ ቢሻሌ በመገንባት ላይ ይገኛል፡፡ ግንባታው የሚካሄደው ኩባንያው ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በሊዝ በገዛው 340,000 ካሬ ሜትር ቦታ ላይ ሲሆን፣ ግንባታውን የሚያካሂደው የቻይና ኩባንያ ነው፡፡ የቤቶቹ ግንባታ 30 በመቶ መድረሱን አቶ ተወልደ ተናግረዋል፡፡
አየር መንገዱ ሠራተኞቹ ከድርጅቱ ጋር እንዲቆዩ እንደሚፈልግ ገልጸው፣ የሠለጠኑ ባለሙያዎች ለምን ወደሌሎች አገሮች እንደሚሰደዱ ለማወቅ በተደረገ ጥናት የመኖሪያ ቤትና መኪና ፍለጋ ከተዘረዘሩ ፍላጎቶች ውስጥ ቀዳሚ ሆነው እንደተገኙ ጠቅሰው የቤት ፍላጎትን ለማሟላት የመኖሪያ ቤቶች ግንባታ መጀመሩን፣ ለሠራተኞች የቤት መኪና ለማቅረብ ከኩባንያዎች ጋር በመነጋገር ላይ እንደሆነ አስረድተዋል፡፡
ለአየር መንገዱ ስኬት ሠራተኛው ትልቁን ሚና እንደሚጫወት የገለጹት አቶ ተወልደ፣ ኩባንያው በነደፈው ራዕይ 2025 የተሰኘው የ15 ዓመት የዕድገት መርሐ ግብር የሰው ኃይል ልማት ፕሮግራም ተቀርጾ ተግባራዊ እየተደረገ እንደሚገኝ አስረድተው፣ የአየር መንገዱን አቪዬሽን አካዳሚ ለማስፋፋት 55 ሚሊዮን ዶላር ኢንቨስት በማድረግ ላይ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡ በዚህም የአቪዬሽን አካዳሚው በዓመት 200 የአቪዬሽን ባለሙያ ያሠለጥን እንደነበር፣ አሁን ግን አቅሙን ወደ 1,000 ማሳደጉን አስረድተዋል፡፡ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ዘመናዊ የካርጐ ተርሚናል በ110 ሚሊዮን ዩሮ ወጪ ለመገንባት በእንስቅቃሴ ላይ ነው፡፡ ለዚህ ፕሮጀክትና ለአውሮፕላን ግዢ የሚውል ብድር ለማግኘት ከፒትኤ ባንክ ጋር በመነጋገር ላይ እንደሆነ ለማወቅ ተችሏል፡፡
‹‹የኢትዮጵያ አየር መንገድ የአፍሪካ አየር መንገድ ነው፡፡ አፍሪካ ውስጥ 46 መዳረሻዎች አሉን፡፡ የብዙ አፍሪካ አገሮች አብራሪዎችና ቴክኒሺያኖች እናሠለጥናለን፡፡ የተለያዩ የአፍሪካ አየር መንገዶች አውሮፕላኖችን እንጠግናለን፡፡ ፒቲኤ ባንክ የአፍሪካ ባንክ ነው፡፡ አፍሪካውያን እርስ በርሳችን መተጋገዝ አለብን፤›› ያሉት አቶ ተወልደ፣ እስካሁን በአፍሪካ አገሮች መካከል የሚደረገው የንግድ ልውውጥ አነስተኛ እንደሆነ ሲያስረዱ፣ ‹‹ኢትዮጵያ ወደ አውሮፓ አበባ በብዛት ኤክስፖርት ታደርጋለች፡፡ በቀን ሁለት አውሮፕላኖቻችን አበባ ጭነው ወደ አውሮፓ ይበራሉ፡፡ አፍሪካዊቷ ጋቦን ግን አበባ የምታስመጣው ከአውሮፓ ነው፡፡ ሥጋ ወደ መካከለኛው ኤክስፖርት እናደርጋለን፡፡ አፍሪካዊቷ አንጐላ ግን ሥጋ የምታስመጣው ከብራዚል ነው፡፡ ከኢትዮጵያ አንጐላ የአራት ሰዓት በረራ ብቻ ሲሆን፣ ብራዚል ግን ሩቅ ናት፤›› ብለዋል፡፡
በአፍሪካ አገሮች መካከል ያለው የንግድ ልውውጥ አነስተኛ በመሆኑ ምክንያት በአፍሪካ አገሮች መካከል ያለው የአየር በረራ ግንኙነት ደካማ እንደሆነ የተናገሩት አቶ ተወልደ፣ ይህ ሁኔታ መለወጥ እንዳለበት አስገንዝበዋል፡፡
የፒቲኤ ባንክ ፕሬዚዳንት አቶ አድማሱ የኢትዮጵያ አየር መንገድ በአፍሪካ ግዙፍና ስኬታማ አየር መንገድ መሆኑን ገልጸው፣ በቅርቡ በማላዊ አየር መንገድ ላይ 49 በመቶ የባለቤትነት ድርሻ መግዛቱንና ከበርካታ አፍሪካ አየር መንገዶች ጋር ተባብሮ የሚሠራ ነው ብለዋል፡፡ ከኢትዮጵያ አየር መንገድ ጋር መሥራት ማለት ከብዙ የአፍሪካ አገሮች ጋር መሥራት እንደሆነ አስረድተዋል፡፡ በቀጣይ ባንኩ ከአየር መንገዱ ጋር በሌሎች ፕሮጀክቶች ላይ አብሮ እንደሚሠራ አቶ አድማሱ ተናግረዋል፡፡
በተያያዘ ዜና ፒቲኤ ባንክ የሐበሻ ሲሚንቶ አክሲዮን ማኅበር ለሚያስገነባው ሲሚንቶ ፋብሪካ የሚውል የ60 ሚሊዮን ዶላር ብድር ፈቅዷል፡፡ ባንኩ 60 ሚሊዮን ዶላር ብድር ቢፈቅድም የሐበሻ ሲሚንቶ የብድር ጥያቄ ወደ 50.5 ሚሊዮን ዶላር ዝቅ እንዲል ተደርጓል፡፡ የብድር ስምምነቱ ነሐሴ 16 ቀን 2005 ዓ.ም. ተፈርሟል፡፡
የሐበሻ ሲሚንቶ ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ መስፍን አቢ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ የሐበሻ ሲሚንቶ ከኢትዮጵያ ልማት ባንክ 1.5 ቢሊዮን ብር ብድር ስምምነት ከሁለት ዓመት በፊት ተፈራርሞ የነበረ ቢሆንም፣ ባንኩ በገጠመው የገንዘብ እጥረት የብድር ውሉ ታጥፏል፡፡ በመሆኑም የሐበሻ ሲሚንቶ ማኔጅመንት የኢትዮጵያ መንግሥት በፈቀደለት መሠረት ለፒቲኤ ባንክና ለሌሎች የተለያዩ ዓለም አቀፍ የገንዘብ ተቋማት የብድር ጥያቄ አቅርቧል፡፡ ለፒቲኤ ባንክ ያቀረበው የብድር ጥያቄ 60 ሚሊዮን ዶላር ሲሆን፣ ከሁሉም ዓለም አቀፍ የገንዘብ ተቋማት ቀድሞ አዎንታዊ ምላሽ መስጠቱን አቶ መስፍን ገልጸዋል፡፡
የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ለሐበሻ ሲሚንቶ 660 ሚሊዮን ብር ለማበደር በመስማማቱ ለፒቲኤ ባንክ የቀረበው የ60 ሚሊዮን ዶላር ብድር ጥያቄ ወደ 50.5 ሚሊዮን ዶላር ዝቅ እንዲል ተደርጓል፡፡ በባንኩና በአክሲዮን ማኅበሩ ኃላፊዎች መካከል ድርድር ተካሂዶ ነሐሴ የብድር ውሉ ተፈርሟል፡፡
ለሐበሻ ሲሚንቶ የፒቲኤ ባንክና የልማት ባንክ የፈቀዱት ብድር የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ እንዲያፀድቀው ቀርቧል፡፡ የሐበሻ ሲሚንቶ አክሲዮን ማኅበር በ30 መሥራች ባለአክሲዮኖች በ600,000 ብር ካፒታል እ.ኤ.አ. በ2008 የተቋቋመ ሲሆን፣ ኩባንያው ካፒታሉን ወደ 775 ሚሊዮን ብር፣ የባለአክሲዮኖችን ብዛት ወደ 16,500 አሳድጓል፡፡ ኩባንያው ለሁለት የደቡብ አፍሪካ ኩባንያዎች 47 በመቶ አክሲዮን ሸጧል፡፡ ፕሪቶሪያ ፖርትላንድ ሲሜንትና ኢንዱስትሪያል ዴቨሎፕመንት ኮርፖሬሽን የተባሉት ኩባንያዎች በ48 ሚሊዮን ዶላር አክሲዮን ገዝተዋል፡፡
ሐበሻ ሲሚንቶ አክሲዮን ማኅበር በፊንፊኔ ዙሪያ ኦሮሚያ ልዩ ዞን (በቀድሞ ምዕራብ ሸዋ) በሆለታ ከተማ በዓመት 1.4 ሚሊዮን ቶን ሲሚንቶ የማምረት አቅም ያለው ፋብሪካ በ125 ሚሊዮን ዶላር ወጪ ለመገንባት በእንቅስቃሴ ላይ ይገኛል፡፡ የፋብሪካውን ግንባታ የሚያከናውነው ኖርዘርን ሔቪ ኢንዱስትሪስ ሊሚትድ የተሰኘ የቻይና ኩባንያ ሲሆን፣ በኅዳር ወር 2004 ዓ.ም. 7.9 ሚሊዮን ዶላር የቅድሚያ ክፍያ ተከፍሎት አንዳንድ የቅድመ ግንባታ ሥራዎች ጀምሮ የነበረ ቢሆንም፣ በልማት ባንክ ብድር መታጠፍ ምክንያት ሙሉ በሙሉ ወደ ግንባታ ሥራ ለመግባት ሳይችል ቆይቷል፡፡
የፋብሪካው ንድፍ ሥራ መጠናቀቁን፣ የግንባታ ቦታ ዝግጅት የጉድጓድ ውኃ ቁፋሮና የጠጠር ማምረቻ ቦታ ዝግጅት ሥራዎች ሲሠሩ እንደቆዩ የገለጹት አቶ መስፍን፣ ኖርዘርን ሔቪ ኢንዱስትሪስ አንዳንድ የብረታ ብረት መሣሪያዎችን ሲያመርት እንደቆየ ተናግረዋል፡፡ የፒቲኤና የልማት ባንክ ብድሮች ከተለቀቁ የፋብሪካው ግንባታ በጥቅምት ወር መጨረሻ እንደሚጀመር፣ ግንባታው በሁለት ዓመት ጊዜ ውስጥ ተጠናቆ ማምረት እንደሚቀጥል አቶ መስፍን አስረድተዋል፡፡
ፒቲኤ ባንክ በያዝነው ሳምንት 29ኛው ዓመታዊ ጉባዔውን በአዲስ አበባ በማካሄድ ላይ ይገኛል፡፡ ጉባዔውን ከኢትዮጵያ የገንዘብና ኢኮኖሚ ልማት ሚኒስቴር ጋር በመተባበር የተዘጋጀ ሲሆን፣ በጉባዔው ላይ ከ20 የአፍሪካ አገሮች የገንዘብ ሚኒስቴርና ባንኮች ተወካዮች ተሳታፊ ይሆናሉ፡፡ ተቀማጭነቱ በቡጁምቡራ ብሩንዲ የሆነው ፒቲኤ ባንክ የተመሠረተው እ.ኤ.አ. በ1984 ዓ.ም. ነው፡፡ ኢትዮጵያ ከመሥራች አገሮች አንዷ ናት፡፡ ባለአክሲዮኖቹ ብሩንዲ፣ ኮሞሮስ፣ ቻይና፣ ጂቡቲ፣ ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጐ፣ ግብፅ፣ ኤርትራ፣ ኢትዮጵያ፣ ኬንያ፣ ማላዊ፣ ሞሪሺየስ፣ ሩዋንዳ፣ ሲሼልስ፣ ሶማሊያ፣ ሱዳን፣ ታንዛኒያ፣ ኡጋንዳ፣ ዛምቢያ፣ ዚምባብዌና የአፍሪካ ልማት ባንክ ናቸው፡፡
የባንኩ ካፒታል ሁለት ቢሊዮን ዶላር ሲሆን፣ የቻይና የአክሲዮን ድርሻ ስድስት በመቶ ነው፡፡ ቻይና የአክሲዮን ድርሻዋን ለማሳደግ ከባንኩ ኃላፊዎች ጋር በመነጋገር ላይ ስትሆን፣ የምትጨምረው የአክሲዮን መጠን በዚህ ሳምንት መጨረሻ ይፋ ይደረጋል ተብሎ ይጠበቃል፡፡
ኢትዮጵያ ከፒቲኤ ባንክ ብዙም እንዳልተጠቀመች የሚናገሩት አቶ አድማሱ፣ ባለፉት አሥር ዓመታት ኢትዮጵያ ከባንኩ ያገኘችው ብድር 30 ሚሊዮን ዶላር ብቻ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡ ባንኩ በኢትዮጵያ የቆዳ ኢንዱስትሪውን ሲደግፍ እንደቆየ አስታውሰው፣ በአሁኑ ወቅት የቡናውን ዘርፍ በማጥናት ላይ እንደሆነ፣ ለግሉ ዘርፍ ለማበደር ከፍተኛ ፍላጎት እንዳለው፣ በኤክስፖርት ላይ ያተኮረ ሥራ የሚሠሩ ኩባንያዎች የፕሮጀክት ዕቅዳቸውን ለባንኩ እንዲያቀርቡ ጥሪያቸውን አስተላልፈዋል፡፡
ኢትዮጵያ ከባንኩ በስፋት ተጠቃሚ ለምን አልሆነችም ለሚለው ጥያቄ ምላሽ የሰጡት አቶ አድማሱ፣ ጥሩ የሆኑ የፕሮጀክት ዕቅዶች አለመቅረብና የባንኩን አቅም ውስንነት እንደ ዋና ምክንያቶች አስቀምጠዋል፡፡ ስለባንኩ ያለው ግንዛቤ አነስተኛ በመሆኑ ባንኩ በተለያዩ አገሮች ስብሰባዎችን በማዘጋጀት ግንዛቤ ለመፍጠር በመሥራት ላይ እንደሚገኝ ያስረዱት አቶ አድማሱ፣ ባንኩ ካፒታሉንና የማበደር አቅሙን ማሳደጉን ተናግረዋል፡፡
በስብሰባው ላይ የተገኙት የኢትዮጵያ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ፕሬዚዳንት ወይዘሮ ሙሉ ሰለሞን፣ ባንኩ ከኢትዮጵያ ጋር ለመሥራት ያሳየውን ቁርጠኝነት አድንቀዋል፡፡ ‹‹እኛ ከባንኩ የምንፈልገው ገንዘብ ብቻ ሳይሆን ባንኩ የልማት አጋራችን እንዲሆን እንፈልጋለን፤›› ያሉት ወይዘሮ ሙሉ፣ የኢትዮጵያ የግል ዘርፍ አቅም የሌለው በመሆኑ ፒቲኤ የብድር ማስያዣ ላይ አስተያየት እንዲያደርግ ጠይቀዋል፡፡ ኢንሹራንስ ኩባንያዎች በብድር ሒደቱ ተሳታፊ በመሆን ፒቲኤ የኢንሹራንስ ኩባንያዎችን የብድር ዋስትና እንዲቀበል ሐሳብ አቅርበዋል፡፡