28/01/2023
አዲስ የተቋቋመው የኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ሲኖዶስ 12 የነባሩን ሲኖዶስ አባላት አወገዘ።
እነዚህ ጳጳሳት ከዲቆንነት ጀምሮ እስከ ሊቀ ጳጳስነት የተሰጣቸው የክህነት ማእረግ እንዲነሳና ከዚህ በኋላ አቶ በሚለው ማእረግ እንዲጠሩ ወስኗል።
የነባሩ ሲኖዶስ አካሄድ ምእመናንና ቤተክርስቲያኗ የሚጠቅም አይደለም፣ የአንድ ቡድንና ወገን መገልገያ ሆኗል ብሏል።
የአዲሱ ሲኖዶስ አባላት ጉዳዩን አስመልክቶ ባወጡት መግለጫ የንጉሠ ነገሥቱ መንግሥት በሚከተለው አንድ ሀገር፣ አንድ ቋንቋ ፖሊሲ በገዢው መደብና በቤተ ክርስቲያን አለቆች ስምምነት ከግዕዝና ከአማርኛ ቋንቋ በቀር ቤተክርስቲያንን ለማገልገል ሳይፈቀድ መቆየቱን አስታውሰዋል።
ይህም የሆነው ከአንድ ጎሳ የሚወለዱ የቤተ መንግሥትና የቤተ ክህነት ገዥዎችን የጥቅም ክፍፍል ለማስቀጠል መሆኑን አስረድተዋል።
በመሆኑም ባለፉት ሰባ ዓመታት የተደራጀው የመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነትና የጳጳሳት ሹመት የወንጌል አገልግሎት ለብሔር ብሄረሰቦች በቋንቋቸው ማድረስ ሳይሆን በአብዛኛው የበለጠ ሥጋዊ ሀብትን ለማደላደል በሚፈልጉ ኤጵስቆጶሳት እየተሞላች መምጣቷን ተናግረዋል።
ቀስ በቀስ የኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ምእመናንን ለቤተ ክርስቲያናቸው እንግዳ እንዲሆኑና ከቤተ ክርስቲያን እንዲርቁ እያደረገ መምጣቱንም አክለዋል።
ይህንን ችግር መፍታት ያልቻለው ነባሩ ሲኖዶስ ይህንን ችግር ለመፍታት እየተጉ ያሉት ሦስቱ ሊቃነ ጳጳሳትና 25-ቱ ኤጲስ ቆጶሳት ላይ ያስተላለፈው ውሳኔ ለቤተ ክርስቲያን የሚቆረቆሩና ለቤተ ክርስቲያን የሚተጉትን ካህናት፣ ዲያቆናትና ምእመናንን ከቤተ ክርስቲያን አርቆ በቤተ ክርስቲያን ውድቀት የተለመደ ሥጋዊ ምቾታቸውንና ጎጠኛ ፍላጎታቸውን ለመምራት እንዲመቻቸው ያለመ መሆኑን አብራርተዋል።
እንዲሁም የአዲሱ ሲኖዶስ ዓላማ እንደ ከሳሾች የዘርና የጎሳ ክፍፍል ለመፍጠር ሳይሆን የኤጲስ ቆጶሳት ሹመት ነው ያሉ ሲሆን የተሾሙት አባቶችም ከሹመታቸው በፊት ቤተክርስቲያን በሰጠቻቸው ልዩ ልዩ ታላላቅ ኃላፊነቶችን ሲወጡ የነበሩና አገልግሎታቸውም በምእመናን ዘንድ የታወቀና የተመሰከረላቸው መሆኑን ጠቅሰዋል።
ከዚህም በላይ ነባሩ የሲኖዶስ አባላት ከቀኖና ውጪ የጵጵስና ሹመት ያደረጉ ሊቃነ ጳጳሳት እንዳሉ እያወቁ በጎጠኝነት ድጋፍ አድርገው በቀኖናው መሰረት የተሾሙትን ኤጲስ ቆጶሳት ማውገዝ ትርጉም የሌለውና እውነተኞች አባቶች ወደ ቅዱስ ሲኖዶስ እንዳይገቡ ለመከላከል የተደረገ መሆኑን አስረድተዋል።
"እራሳቸው እንደገለጹት ውግዘት ካስተላለፉ በኋላ የችግሩን ምንጭ ለማጥናት ኮሚቴ እንዲቋቋም መወሰናቸው የማውገዝ ዓላማቸውን በቶሎ ለመፈጸም እንጂ ችግሩን በትክክል መርምሮ እልባት ለመስጠት አልነበረም" በማለትም አክለዋል።
የግብጽ ቤተክርስቲያን ጭምር አውግዛለች መባሉ ላይም "ለ1,600 ዓመታት ቤተ ክርስቲያናችን ከራሷ ልጆች ጳጳሳት ሹማ በሕዝቦችዋ ቋንቋ እንዳታስተምር ማድረጉዋ እየታወቀ፣ በእስራኤል ሀገር የሚገኘውን የዴር ሱልጣን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ገዳማችንን ለመንጠቅ የምትታገለንን እንደ ደጋፊና ተቆርቋሪ ቆጥሮ የኤጲስ ቆጶሳቱን ምርጫ ተቃወመች መባሉ ምእመናንን ለማሳሳትና ጥንቱንም የኢትዮጵያ ቤተክርስቲያን እንዳትስፋፋ ያደረገችውን እንደ በጎ ተግባር መውሰድ ነው" የሚል ምላሽ ሰጥተዋል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ በልዩ ሁኔታ አሁን የተሰጠውን ሲመት በመቃወም፣ ለክፍፍል ምክንያት በመሆን፣ ቅዱስ ሲኖዶስን በማሳሳትና ሕዝበ ክርስቲያንን ግራ በማጋባት ላይ የተገኙት ያለውን 12 ጳጳሳትን ሲኖዶሱ ከሊቀ ጵጵስና እስከ ድቁና ያለውን ቤተ ክርስቲያን የሰጠቻቸውን ሥልጣነ ክህነት አንስቶ አውግዞ የለያቸው መሆኑንና ከዚህ በኋላ በቀደመ ዓለማዊ ስማቸው "አቶ" ተብለው እንዲጠሩ ምልዓተ ጉባኤው መወሰኑን አሳውቀዋል።
እነዚህም
አቡነ አብርሃም
አቡነ ጴጥሮስ
አቡነ ኤሊያስ
አቡነ ፋኑኤል
አቡነ ናትናኤል
አቡነ ዮሴፍ
አቡነ ዲዮስቆሮስ
አቡነ ሄኖክ
አቡነ መርቆርዮስ
አቡነ ሩፋኤል
አቡነ ሃሪያቆስ
አቡነ ኤሊያስ(ራሳቸውን በስዊድን ጳጳስ አድርገው የሾሙ) መሆናቸውን ሲኖዶሱ አስታውቋል።
በተጨማሪም ሌሎቹ ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳትና ይህን ቅዱስ ሲኖዶስ ለማውገዝ በጉባኤው የተገኙ አባላት ወደ ማስተዋል ተመልሰው እየፈጸሙ ያሉትን ቤተ ክርስትያንን የመክፈል ተግባራቸውን እንዲያጤኑም መክረዋል።
ይሁን እንጂ በያዙት አቋም በመጽናት ቤተክርስትያንን የመክፈል ዓላማቸው ላይ የሚጸኑ ከሆነ ከላይ በተጠቀሱት ግለሰቦች ላይ የተላለፈው ቃለ ውግዘት የሚተላለፍባቸውና በተሳሳተ አቋማቸው ምክንያት ለሚወሰድባቸው ቀኖናዊ እርምት ሃላፊነትን እንደሚወስዱ አሳስቧል።
የቤተ ክርስቲያንን ንብረት ለመጠበቅ ሲባልም በጊዜያዊነት ከዚህ የቅዱስ ሲኖዶስ ውሳኔ በኋላ ማናቸውንም በእጃቸው የሚገኙ የቤተክርስቲያንን ንብረትና ቅርሶች እንዲሁም ለአገልግሎት የሚውሉ ማናቸውንም ንዋየ ቅድሳት ከቦታ ወደ ቦታ እንዳያንቀሳቅሱና እንዳያሸሹ ምዕመናን እና በተለያየ እርከን ላይ ያሉ የመንግስት አካላት ተገቢውን ክትትልና ጥበቃ እንዲያደርጉ ጠይቀዋል።
"በየአህጉረ ስብካታቸው የሚላኩትን ኤጵስ ቆጶሳት በታላቅ ፍቅርና አክብሮት እንድትቀበሉና ለመንፈሳዊ ሕይወታችሁ ማደግ እንድትተጉ" በማለትም ለኦርቶዶክስ እምነት ተከታዮች መልእክታቸውን አስተላልፈዋል።
ዝርዝሩን ለማግኘት : https://omnglobal.com/am/22394/