15/10/2022
በባዕዳን እጅ የገቡት የሥልጣኔ ቁልፎች!
ጥቅምት 04/2015 ዓ.ም (አሚኮ) ኢትዮጵያ በዓለም ታሪክ ቀደምት የሥልጣኔ መነሻ ብቻ ሳትኾን የሰው ልጅ መገኛም ነች፡፡ በዓለም ላይ የራሳቸው ፊደል ካላቸው 18 ሀገራት ውስጥ አንዷ በአፍሪካ ደግሞ ብቸኛዋም ያደርጋታል፡፡ በዚህም አብዛኛው የዓለም ሀገሮች ታሪካቸውን በአፈ ታሪክ ሲያስተላልፉ በነበረበት ዘመን ኢትዮጵያ ፊደልና ቁጥር ቀርጻ፣ ሥዕል ሥላ፣ ታሪክንና ጥበብን ከትባ ለትውልድ ካስተላለፉ ጥቂት የዓለም ሀገራት ውስጥ አንዷ አድርጓታል፡፡ በዚህም የረጅም ጊዜ የዳበረና የጠነከረ የሥልጣኔ ታሪክ ያላት ሀገር መኾኗን መረዳት ይቻላል።
እነዚህን ታሪኮች በመጀመሪያ በድንጋይ፣ በእንጨትና በብረት በኋላም ከልዩ ልዩ እንስሳት ቆዳ በተዘጋጁ ብራናዎች ላይ በመከተብ በዓለም ላይ ባለ ታሪክ ሀገር አድርጓታል።
በእነዚህ የብራና መጻሕፍት የሀገራችን ታሪክ፣ ሥልጣኔ፣ ወግና ሥርዓት፣ ማንነት፣ ቅርሶች፣ መልክዓ ምድር አቀማመጥ፣ ዕጽዋት እና ሌሎችም ተሰንዶባቸዋል፡፡
የዜማ፣ የኪነ ጥበብ፣ ሥነ ሥዕል፣ ቅርጻ ቅርጽ፣ ኪነ ሕንጻ፣ ሥነ ጽሑፍ፣ ሥለ ከዋክብት ጥናት፣ ዘመን አቆጣጠር፣ ስለ አልባሳትና ጌጣጌጥ አዘገጃጀት፣ ስለ ማዕድናት፣ ስለ መድኃኒት ቅመማ፣ ስለ ሥነ ፈለግ፣ የሒሳብ ቀመር፣ ፍልስፍና ወዘተ ያልዳሰሱትና ያላካተቱት ነገር የለም፡፡
እነዚህ መጻሕፍት ዛሬ በዓለም ላይ ለተፈጠረው የሥልጣኔ፣ የሥነ ጥበብ ውጤቶችና ዘመናዊ ባሕል መዳበር ሥር መሠረት እና ፈር ቀዳጆች እንደኾኑም ይነገራል፡፡
ታዲያ ይህንን የሀገራችን የሥልጣኔ ምሥጢር የያዙ መጽሐፍት በተለያዩ ጊዜያት በተለያየ መንገድ ተዘርፈው ወደ ውጭ ሀገራት ተወስደዋል፤ በተነሱ ጦርነቶችም ወድመዋል።
ከ50 ሺህ በላይ የኢትዮጵያ ጥንታዊ መጽሐፍትና ከ100 ሺህ በላይ የኢትዮጵያ ቅርሶችና ጥንታዊ ጽሑፎች በተለያየ ጊዜና መንገድ ተዘርፈው በተለያዩ ሀገራት ውስጥ እንደሚገኙም የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) ከዚህ በፊት ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ማንሳታቸው ይታወሳል፡፡
ጸሐፊ ኃይለማሪያም ኤፍሬም ድብ አንበሳ የኢትዮጵያ ታሪክ፣ ቅርስ፣ ባሕልና የተፈጥሮ መስሕብ በሚል በ2013 ዓ.ም ባሳተሙት መጽሐፍ ተዘርፈው ወደ ውጭ ከተወሰዱት ብራናዎች ውስጥ የተመዘገቡት 6 ሺህ 928 መኾናቸውን ገልጸዋል።
ከተመዘገቡት ውስጥ፦
•በፈረንሳይ 1 ሺህ 50፣
•በእንግሊዝ 930 የሚኾኑ ይገኛሉ፡፡ እነዚህ መጻሕፍት ዐፄ ቴዎድሮስ መቅደላ ላይ ሊያሠሩት በነበረው ቤተ መጻሕፍት እንዲከማቹ ሰብስበዋቸው ስለነበር፤ በጀኔራል ናፒር የሚመራው የእንግሊዝ ጦር በመቅደላ ላይ የሚያወድሙትን አውድመው፣ የቀሩትን ዘርፈዋቸዋል።
•በጀርመን ከ900 በላይ የብራና መጻሕፍት ይገኛሉ፡፡ ጀርመን ከዚህ ባሻገር ለግዕዝ መጻሕፍትና ጥናት የተለየ ትኩረት በመስጠት በሐምቡርግ ዩኒቨርሲቲ ራሱን ችሎ የግዕዝ ጥናት ይሰጣል፡፡
•በጣሊያን 1 ሺህ 300 የሚጠጉ የብራና መጻሕፍት ይገኛሉ፡፡ እነዚህ መጻሕፍት በአብዛኛው በአምስቱ ዓመታት የፋሽስት ወረራ ዘመን የተዘረፉት እንደኾኑ ይነገራል፡፡
• በኢየሩሳሌም 871 ያክል፣
•በሰሜን አሜሪካ ደግሞ 1 ሺህ 80 የሚኾኑት በብዛት የሚገኙበት ነው።
ከእነዚህ ሀገራት ውጭ በሌሎች የአውሮፓና ሌሎች ክፍለ ዓለማት ተበትነው ይገኛሉ፡፡
የፌዴራል ቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር ረዳት ፕሮፌሰር አበባው አያሌው ለአሚኮ እንደገለጹት በርካታ ቅርሶች በተለያዩ አጋጣሚዎች ተዘርፈው ወደ ውጭ ተወስደዋል።
ጣሊያንና ቫቲካን ላይ ከፍተኛ ክምችት እንዳለ ለአብነት አንስተዋል፡፡ በእነዚህ ሀገሮች ከ3 ሺህ በላይ ብራናዎች፣ መስቀሎችና ሌሎች ቅርሶች በወረራው ወቅት በተደራጀ መንገድ የተዘረፉ መኾናቸውን ገልጸዋል፡፡
ሁለተኛው ክምችት ደግሞ ጀርመን ላይ የሚገኘው ቅርስ እንደኾነ ነው የነገሩን፡፡ አክሱም ላይ የአርኪዮሎጂ ቁፋሮ ያካሄዱት ጀርመኖች እንደኾኑ ያነሱት ዳይሬክተሩ በወቅቱ በቁፋሮ የተገኘውን ግኝት ያለማንም ከልካይ መዝረፋቸውን አንስተዋል፡፡ ለማሳየት እንኳ የማይፈልጉት የቁፋሮ ውጤት እንዳለ ነው ያነሱት። እንግሊዝ ፣ አሜሪካ ቤልጅየምና ሌሎች ሀገሮች ላይም በርካታ ቅርስ እንደሚገኝ ገልጸዋል፡፡
ዋና ዳይሬክተሩ እንዳሉት የተዘረፉ ቅርሶችን በባለሥልጣን መሥሪያ ቤቱና ከዚህ በፊት በተቋቋመው ብሔራዊ ቅርስ አስመላሽ ኮሚቴ አማካይነት ለማስመለስ እየተሠራ መኾኑን ገልጸዋል፡፡ በርካታ ቅርሶች የሚገኙበትን ቦታና በምን ኹኔታ እንዳሉ የመለየት ሥራ መከናወኑንም አንስተዋል፡፡
በዚህም መሠረት መንግሥት ቅርሶችን በሦስት መንገድ ለማስመለስ እንደሚሠራ ዋና ዳይሬክተሩ ገልጸዋል፡፡
አንደኛው በዲፕሎማሲ የማስመለስ ሥራ ነው፡፡ ቅርሶች የሚገኙበት ሀገርና ያለበትን ሁኔታ እንጂ እንዴት እንደወጣ የሚያሳይ መረጃ ባለመኖሩ ቅርሱ ከሚገኝበት ሀገር ጋር በሚፈጠር መልካም ግንኙነት የማስመለስ ሥራ እንደሚሠራ አመላክተዋል፡፡
ሁለተኛው መንገድ ደግሞ በሕግ አግባብ ማስመለስ ነው፡፡ ኾን ተብለው መቅደላና ሌሎች አካባቢዎች በእንግሊዝና በጣሊያን ወረራ ጊዜ የተዘረፉ ቅርሶችን በሕግ አግባብ የማስመለስ ሥራ የሚሠራ ይኾናል፡፡
ሀገራቱ እንደ እ.ኤ.አ በ1947 የቅርስ አመላለስ ድንጋጌ ፈራሚ ሀገር እንደመኾናቸው ሕግን ተከትሎ የማስመለስ ሥራ ይሠራል ብለዋል፡፡
ሦስተኛው መንገድ ደግሞ ተቋማትንና ግለሰቦችን በማግባባት የማስመለስ ሥራ እንደሚከናወን ነው የገለጹት።
ከዚህ በፊት በተሠራው ሥራ የአጼ ቴዎድሮስ ቁንዳላ (ሹሩባ) እና ሌሎች ጥንታዊና ታሪካዊ ቅርሶች መመለሳቸው የሚታወስ ነው።
ዘጋቢ፦ ዳግማዊ ተሠራ
ለሀገር ክብር በትግል እናብር‼
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2RnNHCq
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/336LQaS
ቲክቶክ https://bit.ly/32rKF5J