05/05/2022
ኦሞ ራቴ
ቦታው ራቴ ሲባል ወንዙ ደግሞ ኦሞ ነው። ይህ ነው ኦሞ ራቴ ያስባለው። ራቴ ማለት ጋሻ፣ መከታ እና መሸሸጊያ ማለት ነው። በዚህም ለኦሞ ያላቸውን ክብር በሕይወታቸው ብቻም ሳይሆን በመንደራቸውም ስያሜ መግለጻቸውን ለማየት ችለናል።
የመንደሩ ሰላምታ ልውውጥ: አንድ ሰው ኮሚዛብ ብለን ሰላም ስንለው ያ ሰውም ያሚዛብ ብሎ ይመልስልናል።
ብዙ ሰው ተሰብስቦ ስናገኝም ኢቲሚዛብ ብለን ሰላምታ እንሰጣለን እነርሱም ያኚሚዛብ ብለው ይመልሳሉ።
እኛም ከኦሞራቴ ኢቲሚዛብ ብለን ሰላምታን ላክንላችሁ።
ዳሰነች
ወንዙን ተከትለው የሚኖሩ ናቸው። ስምንት ጎሳ አላቸው። አንድ ቋንቋ ተናጋሪ ሲሆኑ ተመሳሳይ ባህልም አላቸው። ኤሌሌ መንደር ነው ያለነው። ይኸውም ከዳር እስከ ዳር ተብሎ ይተረጎማል። አርብቶ አደሮች ሲሆኑ በደረቅ ወቅትም ውሃን ተከትለው ይሄዳሉ። ከብት ይዘው የሚጓዙት ወጣት ወንዶች እና ልጃገረዶች ሲሆኑ እናቶች እና ሕጻናት በመንደሩ ይቆያሉ። የፍየል ወተት ይጠቀማሉ። አህያ እና ለጭነት የሚያገለግሉ የቤት እንስሶች አሏቸው። አንድ ወንድ እስከ አስር ሴት ማግባት ይችላል። ይህ የሚከናወነው ግን በመጀመሪያ ሚስት ፍቃድ ነው።
የተለያየ የፀጉር አሠራር እና የጌጣጌጥ ዐይነት ይጠቀማሉ። ይህም በማህበረሰቡ ያሉበትን የጋብቻ ሁኔታ ይገልጻል።