22/10/2022
ጥቅምት 12 - የንጉሥ ሳህለሥላሴ ወሰንሰገድ የእረፍት እና የንጉሥ ኃይለመለኮት ሳህለሥላሴ የንግሥና መታሰቢያ ቀን … 175ኛ ዓመት መታሰቢያ
ስም ጥሩና ገናናው የሸዋ ንጉሥ፣ ንጉሥ ሳህለሥላሴ ወሰንሰገድ ያረፉት ከዛሬ 175 ዓመታት በፊት፣ ጥቅምት 12 ቀን 1840 ዓ.ም ነበር፡፡ ልጃቸው ንጉሥ ኃይለመለኮት ሳህለሥላሴ (የዳግማዊ አፄ ምኒልክ አባት) ሟቹን አባታቸው ዙፋን የተተኩትም ከዛሬ 167 ዓመታት በፊት፣ ጥቅምት 12 ቀን 1840 ዓ.ም ነበር፡፡
ንጉሥ ሳህለሥላሴ ወሰንሰገድ የራስ ወሰንሰገድ አስፋወሰን እና የወይዘሮ ዘነበወርቅ ጎሌ ልጅ ናቸው፡፡ የተወለዱት በ1788 ዓ.ም ነው፡፡ በዘመኑም ‹‹ኢትዮጵያን አንድ አድርጎ የሚገዛ ምኒልክ የሚባል ንጉሥ ይነግሣል›› የሚባል ንግርት ስለነበር፣ አባታቸው ራስ ወሰንሰገድ ‹‹ምኒልክ›› የሚል ስም አውጥተውላቸው ነበር። አባታቸው ራስ ወሰንሰገድ አስፋወሰን ሲሞቱ ሰኔ 1 ቀን 1806 ዓ.ም በ18 ዓመታቸው የአባታቸውን አልጋ ወርሰው ሸዋን ማስተዳደር ጀመሩ፡፡
ንጉሥ ሳህለሥላሴ ከሸዋ ባላባቶች መካከል (ከነጋሲ ክርስቶስ እስከ ኃይለመለኮት ድረስ ካሉት ገዢዎች መካከል) ኃያሉ፣ ሰፊ ግዛትና ብዙ ሀብት የነበራቸው እንደሆኑ ታሪካቸው ያሳያል፡፡ በወቅቱ በዓለም ላይ ኃያላን ከነበሩት ከብሪታኒያና ከፈረንሳይ መንግሥታትም ጋር የንግድና የወዳጅነት ስምምነት መፈራረማቸውም የዚሁ ኃያልነታቸው ማሳያ ነው፡፡
ንጉሥ ሣህለሥላሴ ሸዋ ገዢ በነበሩበት ጊዜ ኢትዮጵያ በዘመነ መሳፍንት አገዛዝ ላይ ትገኝ ስለነበር አንድ/ጠንካራ ማዕከላዊ መንግሥት ባለመኖሩ እርሳቸው ኃይላቸውን በማጠናከር አንኮበርን መሰረት አድርገው ግሼ፣ ግድም፣ ኤፍራታ፣ አንጾኪያ፣ ይፋት፣ መርሐቤቴ፣ ላምዋሻ፣ ሞረት፣ እንሳሮ፣ አህያፈጅ፣ ቀይ አፈር፣ ቡልጋ፣ ምንጃር የተባሉትና አፋር ድረስ ያሉ ብዙ ቦታዎች በአስተዳደራቸው ስር እንዲሆኑ አድርገው ነበር።
ንጉሥ ሳህለሥላሴ በአስተዳደር ዘመናቸው የተቸገረን የሚረዱ፤ አቅም ላጣ ግብሩን የሚምሩ፤ ዕዳ ላለበት ዕዳውን የሚከፍሉ እንዲሁም ጥማድ በሬ ለሌለው ጥማድ እየሰጡ እረስ ቆፍር እያሉ ሕዝባቸውን ለሥራ የሚያበረቱ ነበሩ። እነዚህን በመሳሰሉ መልካም ሥራቻቸው የተነሳም በሕዝቡ ዘንድ በጣም ይወደዱ እንደነበር ታሪካቸው ያስረዳል።
የአሁኗ አዲስ አበባም ገና ከመመስረቷ በፊት ንጉሥ ሣህለሥላሴ መንግሥታቸውን (ግዛታቸውን) ለማስፋት በሚንቀሳቀሱበት ጊዜ አሁን የምኒልክ ቤተመንግሥት ወደሚገኝበት አካባቢ መጥተው ድንኳን ተክለው በመቀመጥ ‹‹አንቺ ቦታ የልጅ ልጄ ትልቅ ከተማ ይቆረቁርብሻል … የልጅ ልጄ እዚች ቦታ ላይ ከተማ ይሰራባታል›› ብለው ትንቢት ተናግረው እንደነበር ይባላል። ይህ ትንቢታቸውም የልጅ ልጃቸው በሆነት ንጉሰ ነገሥት ዳግማዊ አፄ ምኒልክ ፍጻሜ አገኘ (እውን ሆነ)።
በመጨረሻም ንጉሥ ሣህለሥላሴ ለ33 ዓመታት ከ 5 ወራት ያህል ሸዋንና በሸዋ ዙሪያ ያለውን ቦታ ሲያስተዳድሩ ቆይተው ከዛሬ 175 ዓመታት በፊት (ጥቅምት 12 ቀን 1840 ዓ.ም) ደብረ ብርሃን ከተማ ላይ ከዚህ ዓለም በሞት ተለዩ። ስርዓተ ቀብራቸውም ራሳቸው ባሰሩት በአንኮበር ቅዱስ ሚካኤል ቤተ ክርስቲያን ተፈፅሟል።
የንጉሥ ሳህለሥላሴን ሞት ተከትሎ ዙፋኑን የወረሱት ልጃቸው ንጉሥ ኃይለመለኮት ሳህለሥላሴ ነበሩ፡፡ የንጉሥ ኃይለመለኮት እናት ወ/ሮ በለጥሻቸው ወልዴ ይባላሉ፡፡
ንጉሥ ኃይለመለኮት በሰውነታቸው ግዝፈትና ጥንካሬ እንዲሁም በልባቸው ቀናነት በሸዋ ዘንድ የታወቁና የተወደዱ ንጉሥ ነበሩ። ብላቴን ጌታ ኅሩይ ወልደሥላሴ ‹‹የኢትዮጵያ ታሪክ›› በሚለው መጽሐፋቸው እንደሚነግሩን ንጉሥ ኃይለመለኮት ከጥንካሬያቸው የተነሳ ኢላማ ተኩስ በሚተኩሱ ጊዜ መሳሪያውን አጠንክረው በመያዛቸው ምክንያት ጥይቱ ሲወጣ ጠመንጃቸው ለሁለት ተሰብሮ እጃቸው ላይ ቀርቶ ያውቃል።
ንጉሥ ኃይለመለኮት ሸዋን ለ8 ዓመታት አስተዳድረዋል። በስልጣን ላይ ሳሉም ተቀናቃኝ ሊሆኑባቸው የሚችሉትን ወገኖቻቸውን እንዲያስሯቸውና እንዲያስወግዷቸው ሰዎች ሲመክሯቸው፣ ‹‹ተዉ! ይሄን አላደርገውም! እግዚአብሔር የወደደውን ነው የሚያስገዛው›› የሚሉ ቀና ሰው እንደነበሩ ብላቴን ጌታ ኅሩይ ወልደሥላሴ በመጽሐፋቸው ጠቅሰውታል።
በመጨረሻም ዳግማዊ ዐጼ ቴዎድሮስ በሀገሪቱ በየቦታው ያለውን የተከፋፈለ አገዛዝ ወደ አንድ አስተዳደር በማምጣት በማእከላዊ መንግሥት ስር የምትተዳር አንዲት ሀገር ለመመስረት አስበው ከየመሳፍንቱ ጋር በሚዋጉበት ጊዜ ‹‹ንጉሰ ነገሥቱ ወደ ሸዋም ሊመጡ ነው›› የሚል ወሬ ተሰምቶ ንገሥ ኃይለመለኮትም ለጦርነት ተዘጋጁ፤ ሆኖም ግን ከጦርነቱ ቀደም ብሎ ንጉሥ ኃይለመለኮት ታመው ነበርና እርሳቸው በጦርነቱ ሳይካፈሉ፣ ጥቅምት 30 ቀን 1848 ዓ.ም ከዚህ ዓለም በሞት ተለዩ፡፡
(ልዑል አምደ ፅዮን)
(የደብረብረሃን ቱሪዝም ልማት ፕሮግራም)