25/03/2024
ሶፍ ኡመር ዋሻ
በሀገራችን የቱሪዝም መስህቦች መገኛነት አንጋፋውን ስፍራ ከሚይዙ አካባቢዎች አንዱ የሆነው የባሌ ዞን እጅግ በርካታ የሆኑ የቱሪዝም መዳረሻ ስፍራዎችን የታደለ ምድር ነው፡፡ ከመስህቦቹ ውስጥም የሚያስገርም የተፈጥሮ ስጦታ የሆነውና በአፍሪካ ካሉ ትላልቅ ዋሻዎች አንዱ የሆነው የሶፍ ኡመር ተፈጥሮአዊ ዋሻ ይገኝበታል፡፡ 15.1 ኪ.ሜ. ርዝመት ያለው ይህ ዋሻ በኢትዮጵያም ረጅሙ እንደሆነ ይነገርለታል፡፡ ዋሻው በጊዜያዊ የዓለም ቅርስነት ተመዝግቧል፡፡
ዋሻው በእስልምና እምነት ተከታዮች ዘንድ መንፈሳዊ ትርጉም የሚሰጠው ስፍራ ነው፡፡ ስያሜውን ያገኘው ሶፍ ኡመር ከሚባሉ የሀይማኖት ሰው ነው፤ ሶፍ ኡመር ዋሻውን በመጠለያነት በመጠቀም ለብዙ ዓመታት ኖረዋል፡፡ ወደ ዋሻው መግቢያ በድንጋይ የታጠረ ቦታ ክር ቅዱስ ኡመር ይባላል፡፡ ይኸውም ከበሮ በመምታት የሚያመሰግኑበትና የስለት ከብት በማረድ የሚበላበት ቦታ ነው፡፡ የሚሳሉ ሰዎች ከታረደው በግ /ፍየል/ ላይ ትንሽ ቆዳ ተቆርጦ ዋሻ ውስጥ ለፀሎት ይንጠለጠልላቸዋል፡፡ በስተቀኝ በኩል ከዋሻው ፊት ለፊት ወንዙ ውስጥ በጣም ትልቅ የሆነ የተከፈተ መሶብ ቅርፅ ያለው ተፈጥሮ የተራቀቀበት ወጥ ድንጋይ ሆነ የሶፍ ኡመር መቀመጫ አለ፡፡
የሶፍ ኡመር ዋሻ መግቢያ ጉለንተናየው መኩ ሲባል መውጫው ደግሞ ሁልቃ ይባላል፡፡ ጉለንተናየው መኩ የሶፍ ኡመር ልጅ ከራዮሞኩ የምትቀመጥበት ቦታ ነው፡፡ የባትሪውን መብራት በሚሰብረው ጨለማ ወደ ዋሻ ውስጥ ሲገባ ጀባ ቢቂላ የሚባል ትልቅ ክብ ድንጋይ አለ፡፡ በዚህ ቦታ ከድንጋዩ በላይ ግንድ የነበረ ሲሆን ግንዱ ላይ አናትና አባት የረገሟቸው በጣም የሚያስቸግሩ ወጣቶች የሚታሰሩበት ቦታ ነው፡፡ ጀባ ቢቂላ የተባለው በወቅቱ ከታሰሩ ወጣቶች አንዱ ነው፡፡ ጥፋተኞቹ የሚወጡበት ትልቁና ክቡ ድንጋይ በጀርባው በኩል የኢትዮጵያ ካርታን ቅርፅ ይዟል፡፡
ዋሻው የተለያዩና በርካታ ክፍሎች ሲኖሩት ወደ መሀል ሰፊ የሆነው ክፍል አለይህም ፊጢ ሱማ አብዲ ይባላል፡፡ በሶፍ ኡመር ልጅ ስም የተሰየመ ቦታ ነው፡፡ ክፍሉ /አዳራሹ/ መካከል ላይ በክብ ቅርፅ ጎርጎድ ብሎ ወደ ላይ ከፍ ያለ ሲሆን ተፈጥሮአዊ መሆኑ ያስገርማል፡፡
የተለያዩ ገፅታዎችን በማሳየት አንዱን አድንቀን ሳንነሳ ሌላ የተፈጥሮ ገፅታን የሚያሳየን የማያልቅበት ይህ ዋሻ የሶፍ ኡመር አዳራሽ ተብሎ ወደ ተሰየመው ዋሻ ክፍል ያሸጋግረናል፣ በዚህ ክፍል ችግር ያለባቸው ሰዎች ከሶፍ ኡመር ጋር ተገናኝተው ችግራቸውን የሚያስረዱበት ቦታ ነው፡፡ ሌላው አስገራሚው የዋሻ ክፍል ደግሞ ስጋጃ የተባለው ነው፡፡ ይህ ክፍል መስገጃ ሲሆን በዚህ ክፍል አራት ትልልቅ ጠፍጣፋና ሰፋፊ ድንጋዮች አሉ፣ እነዚህም የሶፍ ኡመር፣ የሼህ ሁሴን፣ የከራዩ መኮ እና የሼህ አበል ቃሲም መስገጃ ስጋጃዎች ናቸው ፡፡
ይሄ ግዙፍ ዋሻ ከአዕምሮ የማይጠፋና እጅግ አስገራሚ የሆነ ተፈጥሮ ኪናዊ ጥበብን ያሳየችበት ስራ ነው፡፡ ጣራው የፋብሪካ ምርት የሆነ ልምድ ባለው ባለሙያ ተስተካክሎ የተገጠመ ወጥ ኮርኒስ ይመስላል፡፡ በዋሻው መሀል የሚጓዘው ዌብ የተሰኘው ወንዝ በውስጡ ሲጓዝ ሰባት ጊዜ የሚታጠፍባቸው ቦታዎች አሉ፡፡ ሁለቱም ተጣምረው መኖራቸው በራሱ አስገራሚ ትዕይንት ነው፡፡