31/01/2023
ʺ ደብረ ታቦር እልል ትላለች፤ አጅባር በደስታ ትዋጣለች"
ጥንታዊቷ ከተማ በእልልታ ትዋጣለች፣ አምላክን እያመሰገነች እልል ትላለች፣ ጎዳናዎቿ ይባረካሉ፣ ነጫጭ በለበሱ ምዕመናን ይመላሉ፣ ጎበዛዝቱ ትጥቃቸውን አሳምረው በኩራት ይወጣሉ፣ በአስፈሪ ግርማ ይረማመዳሉ፣ ወይዛዝርቱ ኢትዮጵያዊነት በበዛበት ውበት ተውበው ልብን በሚያስደነግጥ ደም ግባት ይታያሉ፣ አጅባር በደስታ ትዋጣለች፣ በምስጋና ትመላለች፣ በእልልታና በዝማሬ ከፍ ከፍ ትላለች፣ ፈረሳቸውን በሸለሙ ጀግኖች ትከበባለች፡፡
ዓይኖች ጥንታዊቷን ከተማ ያያሉ፣ ጀሮዎች ወደ ጥንታዊቷ ከተማ ያዘነብላሉ፣ እግሮች ወደ ጥንታዊቷ ከተማ ይጓዛሉ፣ በታቦር ተራራ የተሰየመችው፣ የነገሥታቱን፣ የመኳንንቱን፣ የመሳፍንቱን ቀልብ የሳበችው፣ለሊቃውንቱ፣ ለዲያቆናቱ፣ ለዘማሪያኑና ለአንባቢያኑ ማረፊያ የኾነችው ከተማ በአራቱም ንፍቅ በሚመጡ እንግዶች ትደምቃለች፡፡
ሊቃውንቱ ምድራዊ የማይመስለውን፣ ሰማያዊ የሚመስለውን፣ በምድርም በሰማይም የተወደደውን ምስጋና ያቀርባሉ፣ ያለድካም አምላካቸውን ያመሰግናሉ፣ ለምድር ሰላሙን እና በረከቱን ይለምናሉ፣ ዲያቆናቱ በትሕትና ለተልዕኮ ይፋጠናሉ፣ ለአበው ሊቃውንት እጅ እየነሱ ይታዘዛሉ፣ ነጫጭ የለበሱ ምዕመናን እልል እያሉ ወደ ቤተመቅደስ ይጓዛሉ፣ለጌታ ክብር የተገባውን መባ እየያዙ ይገሰግሳሉ፣ እጅ እየነሱ በአጸዱ ሥር ይሰባሰባሉ፡፡
ኃያላኑ ስለ ሀገር ፍቅር፣ ስለ ሠንደቅ ክብር መክረውባታል፣ በብልሃትና በጥበብ ሀገር መርተውባታል፣ የሀገር አንድነትን አጽንተውባታል፣ የኢትዮጵያዊነትን ልክ፣ የጀግንነትን ዳር አሳይተውባታል፡፡ ጎበዛዝቱ በተራራዎቹና በሸንተረሮቹ ተመላልሰውባታል፣ በሜዳው በፈረሶቻቸው ሽምጥ ጋልበውባታል፣አንደኛው ከሌላኛው ልቆ ለመገኘት ተፎካክረውባታል፡፡
የእግዚዓብሔር መልዐክ የሚመራቸው ሁለት ወንድማማቾች ነበሩ፤ አምላካቸውን በልባቸው ይጠብቁታል። አብዝተው ያመሰግኑታል። በፍቅር ይገዙለታል። እርሱም አብዝቶ ይወዳቸዋል። ይጠብቃቸዋል። ቄስ ወንድማሆም እና ቄስ ዘ ጊዮርጊስ ይሰኛሉ፡፡ እነዚህ ካህናትም አምላካቸውን የሚፈሩ፣ ሃይማኖታቸውን የሚያከብሩ ደጋጎች ነበሩ፡፡ ለታሪክ ተመርጠዋል፣ ደብር ይደብሩ፣ ቤተ እግዚዓብሔርን ያከብሩ ዘንድ ታጭተዋል፡፡ ለእነዚህ የተመረጡ ወንድማማቾች የእግዚዓብሔር መላዕክ ሁለት ፅላት ሰጣቸው፡፡ ፅላተ ጽዮንና ፅላተ ማርያምን። ከሸዋ መንዝ ተነስተው ታቦተ ማርያምን እና ታቦተ ጽዮንን ይዘው ወደ ስሜን በጌምድር አቀኑ፡፡ የእግዚዓብሔር መላዕክ በመንገዳቸው ኹሉ ይጠብቃቸውና ይመራቸው ነበር። ረጅሙን መንገድ ተጉዘው ደብረ ታቦርም ደረሱ፡፡
በዚያ ዘመን አጼ ሰይፈአርድ ነግሠው ኢትዮጵያን ያሥተዳድሩ ነበር፡፡ የመንበረ ንግሥት ቅድስት ልጅቱ ማርያም ቤተክርስቲያን የሰንበት ትምህርት ቤት ተጠሪ ዲያቆን በልአንተ ተመስገን እንደነገሩኝ አጼ ሰይፈአርድ በኢየሱስ ቤተክርስቲያን አቅራቢያ ነበሩ፡፡ እኒያ ደጋግ ሰዎችም ደግሞ ደብረ ታቦር መጥተው በአንድ ሥፍራ ተቀምጠዋል፡፡ አፄ ሰይፈ አርድም ዓይናቸውን ባማተሩ ጊዜ በአንድ ሥፍራ ጭስ ሲጨስ ይመለከታሉ፡፡ ይህም ጭስ ከአንድ ሥፍራ በተደጋጋሚ ሲጨስ ተመለከቱ፡፡ የጦር አበጋዛቸውንም ጭስ የሚጨስበትን አካባቢ አስሶ ይመጣ ዘንድ አዘዙት፡፡
የጦር አበጋዛቸውም ጭስ ወደ ሚጨስበት ስፍራ ባቀና ጊዜ እኒያን ወንድማማቾች ካህናት አገኛቸው፡፡ ሰላምታ ሰጥቶም ጠየቃቸው፣ ካህናቱም ለታቦታቱ ማረፊያ የሚኾን ቤተ መቅደስ ማነጽ እንደሚሹ ነገሩት፡፡ እርሱም ያሰቡት ይሳካ ዘንድ ፈቀደላቸው፡፡ አምላካቸው ይፈቅድ ዘንድ ተማጸኑ፡፡ አምላክም ራዕይ አሳያቸው፣ ቤተ መቅደስ የሚያንጹበትን ሥፍራ አመላከታቸው፡፡ ለታቦተ ማርያም ቤተ መቅደስ አንጸው ቅዳሴ ቤቱን አከበሩ፡፡ ታቦተ ጽዮን የምታርፍበት ቤተ መቅደስ የሚያንጹበት ሥፍራም ፈለጉ፡፡ ለአንድ ዓመት ከአራት ወራትም ቆዩ፡፡
ካህናቱ ራዕይ አዩ፡፡ ለታቦተ ጽዮን መጀመሪያ መጥተው ካረፉባት ሥፍራ ቤተ መቅደስ ይታነጽ ዘንድ ተመለከቱ፡፡ ያንንም አደረጉ፡፡ የአብያተ መቅደሱ አሠራር በአንድ ዓመት ከአራት ወራት ስለሚለያዩ ለአብያተ ክርስቲያናቱ ስያሜ እናውጣ በተባለ ጊዜ የሀገሬው ሰው ቀድማ የተሠራችውን እናቲቱ ማርያም፣ ቆይታ የተሠራችውንም ልጅቱ ማርያም እንበላቸው አሉ፡፡ ተባሉም፤ ያ ስምም እነኾ ዛሬ ድረስ ዘልቋል፡፡ ስሙም ለአብያተ ክርስቲያናቱ ስያሜ ይኾን ዘንድ ወጣ እንጂ በሃይማኖት አስተምህሮስ ልጅቱና እናቲቱ የሚባል የለም ይላሉ አበው፡፡
እኒህ ጥንታዊ አብያተ ክርስቲያናት ታሪክን እየነገሩ፣ ሃይማኖትን እያስተማሩ የሚኖሩ ናቸው፡፡ ከጊዜ በኋላ በራዕይ በተሠራችውና በጥበብ በታነጸችው በመንበረ ንግሥት ቅድስት ልጅቱ ማርያም ቤተክርስቲያን ታቦተ መርቆሬዎስ ገባ፡፡ የሰማዓቱ መርቆሬዎስ ታቦት በዚያች ደብር በመግባቱ በዓለ መርቆሬዎስ በታላቅ ሃይማኖታዊ ሥርዓት ይታሰብባታል፡፡ በወረኃ ጥር በሃያ አምስተኛው ቀን ደብረ ታቦር በበዓለ መርቆሬዎስ ትደምቃለች፡፡ ከፍ ከፍም ትላለች፤ የሊቃውንት እና የምዕመናን ዝማሬ ከፍ ብሎ ይሰማባታል፣ የጎበዛዝቱ ግርማ ይከባታል፣ የወይዛዝርቱ ደም ግብዓት ያስጌጣታል፡፡
የደብረ ልዑላን መንበረ መንግሥት መድኃኔዓለም ቤተክርስቲያን የአራቱ ጉባዔያት መምህር መምህራን በጽሃ ዓለሙ በዓለ መርቆሬዎስ በደብረ ታቦር በታላቅ ሃይማኖታዊ ሥርዓት ይከበራል ብለዋል፡፡ ሊቃውንት ሃይማኖታዊ ሥርዓቱን ሲያደርሱ፣ ምዕመናን በፈረስ ያስቡታል፣ ታቦቱን ያጅቡታል፣ ያመሰግኑታል፡፡
ፈረስ አበው ጋማውን ጭራ እያደረጉ ይዋቡበታል፣ ጭራውን ማሲንቆ እያሠሩ አዝማሪዎች አምላካቸውን ያመሰግኑበታል፣ ነገሥታቱን ያደንቁበታል፣ ደስታቸውን ይገልጹበታል፣ የአዘነውንም ያጽናኑበታል፡፡ ፈረስ ከጠጠር ጋር እህል ሲሰጠው እህሉን መርጦ ይመገባል፣ ሰውም በሕይዎት ሲኖር ከበርካታ መጥፎ ነገሮች መልካሙን እያወጡ መሥራት እንደሚገባ ያመላክታልም ነው የሚሉት የኔታ፡፡
የመርቆሬዎስ ታቦት ከመንበሩ በወጣ ጊዜ፤ ከየአቅጣጫው የመጡ ፈረሰኞች ፈረሶቻቸውን ሦስት ጊዜ ያሰግዳሉ፤ ምስጋናም ያቀርባሉ፣ የቅዱስ መርቆሬዎስ ፈረሰኞች ይባላሉ፣ ከቅዱስ መርቆሬዎስ በረከት ለመሳተፍ ታቦቱን በፈረስ ያጅባሉ፡፡ ፈረሱን ወደ ታቦቱ ሳያሰግዱ አይጋልቡም፣ ከሰገዱ በኋላ ነው የሚያጅቡት ነው ያሉኝ፡፡ ለታቦቱ ማሰገዱ ከአባቶች የቆዬና ሃይማኖታዊ ክብር በመኾኑ ሳይቀንስ መቀጠል አለበት ይላሉ የኔታ በጽሃ፡፡
በዓለ መርቆሬዎስ በደረሰ ጊዜ መንበረ ንግሥት ልጀቷ ማርያም ቤተክርስቲያን በሊቃውንት ትመላለች፣ አጸዷ ሥር ምዕመናኑ ይሰባሰባሉ፡፡ ታቦቱ ከመንበሩ ሲወጣ እልልታው ይደምቃል፣ ምስጋናው ያይላል፣ ፈረሰኞች ያጅቡታል፣ በታላቅ ክብር ወደ ታሪካዊ አጅባር ሜዳ ይወርዳል፤ በማደሪያውም ያርፋል፡፡ አጅባር በሊቃውንት እንደተመላች፣ በመልካሙ ማዕዛ እንደታወደች፣ በምዕመኑ እንደታጀበች ታድራለች፡፡
በነጋም ጊዜ ፈረሰኞቹ ታቦታቸውን በክብር ያጅቡ ዘንድ ይሰባሰባሉ፣ አምሳለ እርግብ የመሰሉ ምዕመናን ነጫጭ ለብሰው፣ ጎዳናዎችን ሞልተው ወደ አጅባር ሜዳ ይጓዛሉ፤ በአጅባር ሜዳ ጀግኖቹ በፈረሶቻቸው ተቀምጠው ሽምጥ ይጋልባሉ፣ አጅባር በጀግኖቹ ትጨነቃለች፣ ምድር በደስታ ትዋጣለች፣ መልካሙን ነገር ታያለች፡፡ በደብረ ታቦር ዩኒቨርሲቲ የአለቃ ገብረሃና የባሕል ጥናት ዳይሬክተርና የታሪክ መምህሩ መሠረት ወርቁ በአጅባር ሜዳ ነገሥታቱ፣ መኳንንቱ፣ መሳፍንቱ እና የጦር አበጋዞች የፈረስ ጉግስ የሚያዩበት፣ የሚጫወቱበት፣ ሽምጥና የፈረስ ላይ ውጊያ ልምምድ የሚያደርጉበት ጥንታዊ ታሪክ ያለው ነው ይሉታል፡፡
በበዓለ መርቆሬዎስ በቀደመው ዘመን ፈረሰኞች ያደርጉት የነበረው አኹንም ይደረጋል፣ በጦር መትቶ ራሱን በጦር ይከላከላል፣ መትቶ ከጠላት ራሱን ያርቃል፣ ጀግኖች አባቶች በጦር ሜዳ ያደርጉት የነበረውን የጦር ስልት በአጅባር ያሳያሉ፡፡ ጀግኖች የጦር ልብሳቸውን ይለብሳሉ፣ ጋሻና ጦራቸውን ይይዛሉ፣ ፈረሳቸውን ሸልመው በአጅባር ሰማይ ሥር እንደ አሻቸው ይኾናሉ፡፡ አጅባር በሰው ተጨንቃ ትውላለች፣ ሰዓቱ በደረሰም ጊዜ ታቦተ መርቆሪዎስ በታላቅ አጀብ ወደ መንበሩ ይመለሳል፡፡
ደጋጎቹ ደግሰዋል፣ አዳራሹን አሳምረዋል፣ ስሞት አፈር ስኾን እያሉ ማብላትና ማጠጣት ያውቁበታል፡፡ እንግዳ ያቀማጥላሉ፣ ሂዱ ጥንታዊቷ ከተማ ደግሳለች፣ እጆቿን ዘርግታ ትቀበላችኋለች፤ ሂዱ ሃይማኖትን፣ ጀግንነትን፣ እሴትን፣ አንድነትን፣ ባሕልን እና ኢትዮጵያዊነትን ከአጅባር ሰማይ ስር ተመልከቱ፡፡
ተፃፈ በታርቆ ክንዴ
አማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን
ደብረታቦር ኮሙኒኬሽን ጥር 22 ቀን 2015 ዓ/ም